Search

የመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ልደት ምስክሮች፦ ሰባሰገል

ማክሰኞ ታኅሣሥ 28, 2018 249

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሰረት “የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ” ልደት በሰውልጆች ታሪክ ውስጥ ትልቁና ድንቅ የሆነ ክስተት እንደሆነ ታስተምራለች። እርግጥ ይህ ክስተት በክርስቲያኖች ሁሉ ድንቅ ስለመሆኑ ይታመናል ደግሞም የአስተምህሮ ማዕከል ሆኖ ይገኛል። ይህ ልደት የተከናወነው በይሁዳ ቤተልሔም ውስጥ በከብቶች በረት ቢሆንም፣ ሰማያዊና ምድራዊ ፍጥረታትን ያስተባበረ ታላቅ ምስጢር የታየበት ስለመሆኑ የእምነቱ አስተምህሮ ይገልጻል።

ነቢያት አስቀድመው “ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች” ብለው የተነበዩት ትንቢት የተፈፀመበት ቅጽበት ነው። በዚያች ሌሊት “የሰላም ንጉሥ” በመወለዱ ሰማያዊያን መላእክት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ” እያሉ በመዘመር የደስታ ብሥራታቸውን ለዓለም አውጀዋል። ይህ ልደት ለሰው ልጆች ሁሉ የድኅነት መንገድን የከፈተና የእግዚአብሔርን ፍቅር ለፍጥረት ሁሉ የገለጸ መለኮታዊ ድርጊት ሆኖ እስከ ዛሬ ይከበራል።

በዚሁ ታላቅ የልደት ታሪክ ውስጥ ጎልተው የሚታዩት “ሰባሰገል” ወይም የጥበብ ሰዎች በመባል የሚታወቁት ከምሥራቅ የመጡት ነገሥታት እንደሆኑ የሃይማኖቱ ትምህርት ነው። እነዚህ ነገሥታት ከሩቅ አገር የክርስቶስን ልደት የሚጠቁም ልዩና ብሩህ ኮከብ በሰማይ ላይ ስላዩ ነበር። ኮከቡን በመከተል ረጅም መንገድ የተጓዙት ለምድራዊ ንጉሥ ክብር ለመስጠት ሳይሆን፣ የዓለም መድኃኒት ለሆነው ሕፃን ለመስገድ ነው። የእነሱ ጉዞ የእምነትና የጽናት ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን፣ አሕዛብም የክርስቶስን አዳኝነት እንዲያውቁ የእግዚአብሔር ጥሪ መሆኑን ያሳያል። እነዚህ ነገሥታት ጥበብንና ሥልጣንን ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በማቀናጀት ለታላቁ ንጉሥ ለመስገድ ብዙ መንገድ በበረሃውን እና ጋራውን አልፈው ቤተልሔም ደርሰዋል።

ሰባሰገሉ ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናል” በማለት በጠየቁ ጊዜ ንጉሥ ሄሮድስና መላው ከተማ ደንግጠው ነበር። ሄሮድስ ለሥልጣኑ በመስጋት ሕፃኑን ለመግደል ቢፈልግም፣ ሰባሰገሉ ግን በመሪው ኮከብ አማካኝነት ሕፃኑ ወዳለበት በረት መሪነትን አግኝተዋል። ኮከቡ ሕፃኑ ባለበት ቦታ ላይ ቆሞ ሲያዩት እጅግ ታላቅ ደስታ ተሰማቸው። ይህ ኮከብ ተራ የሥነ-ፈለክ ክስተት ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር መለኮታዊ መሪነት ለሰው ልጆች ሁሉ የተገለጠበት ምልክት ነበር። ወደ ቤቱ በገቡም ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፣ ወድቀውም ሰገዱለት፣ ይህም አምላክነቱንና ንጉሥነቱን ያረጋገጡበት ትልቅ ተግባራቸው ነበር።

እነዚህ ነገሥታት ለሕፃኑ ክርስቶስ ያቀረቧቸው ስጦታዎች ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ ነበሩ፤ ይህም እያንዳንዳቸው ጥልቅ ምስጢራዊ ትርጉም አላቸው። ወርቅ ማቅረባቸው ለንጉሥነቱ ማረጋገጫ ሲሆን፣ ክርስቶስ የዘላለም የነገሥታት ንጉሥ መሆኑን ያመለክታል። ዕጣን ደግሞ ለአምላክነቱ የቀረበ መሥዋዕት ሲሆን፣ እርሱ እውነተኛ የሰው ልጆች ጸሎት የሚቀርብለት አምላክ መሆኑን ያስረዳል። ከርቤው ደግሞ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል ለሚቀበለው መከራና ሞት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። እነዚህ ሦስት ስጦታዎች ክርስቶስ ንጉሥ፣ አምላክና ቤዛ መሆኑን በአንድነት የሚመሰክሩ ሰማያዊ ምስጢራት ናቸው። ሰባሰገሉ እነዚህን ስጦታዎች በማቅረብ ሀብታቸውንና ጥበባቸውን ለፈጣሪያቸው አስገዝተዋል ተብሎ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ይታመናል።

ከስግደቱና ከስጦታው በኋላ ሰባሰገሉ ወደ አገራቸው የተመለሱት በመጡበት መንገድ ሳይሆን በሌላ መንገድ ነበር። ይህም የሆነው ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ስላሰበ፣ እግዚአብሔር በሕልም “ወደ ሄሮድስ አትመለሱ” ብሎ ስላዘዛቸው ነው። ይህ ድርጊት አማኝ ክርስቶስን ካገኘ በኋላ የቀድሞውን የኃጢአት መንገድ ትቶ በአዲስ የሕይወት መንገድ መጓዝ እንዳለበት ያስተምራል። ሰባሰገሉ ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዥ በመሆን ሕፃኑን ከክፉ እጅ እንዲጠበቅ ረድተዋል። የእነሱ ታሪክ እምነት፣ ታዛዥነትና መለኮታዊ ጥበቃ እንዴት እንደሚሰሩ የሚያሳይ ትልቅ ምስክርነት ተደርጎም ይወሰዳል። ወደ አገራቸው ሲመለሱም ያዩትንና የሰሙትን ድንቅ ነገር ለወገኖቻቸው በማብሰር የመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ልደት ምስክሮች ሆነዋል።

በክርስቲያኖች ዘንድ የክርስቶስ ልደትና የሰባሰገል ጉዞ የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር የታረቀበትና የብርሃን ዘመን መጀመሩን የሚያበስር ነው። የቤተልሔሙ በረት ዝቅታንና ትሕትናን ሲያስተምር፣ የሰባሰገሉ ጉዞ ደግሞ እውነተኛ ጥበብ ፈጣሪን ወደ ማወቅ እንደምትመራ ያሳያል። ይህ ታሪክ በየዓመቱ ሲከበር እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ወሰን የሌለው ፍቅር በማስታወስም ጭምር ነው። እንደ ክርስትና አስተምህሮ ምዕመናን እንደ ሰባሰገሉ ሁሉ የልባቸውን ወርቅ (ፍቅርን)፣ ዕጣን (ጸሎትን) እና ከርቤን (ትዕግሥትን) ለፈጣሪያቸው ማቅርብ እንዳለባቸው ያሳውቃል። የክርስቶስ ልደት የጨለማው ዓለም ብርሃን የወጣበትና የሰው ልጅ ተስፋ የታደሰበት በመሆኑ፣ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በሰው ልጆች ልብ ውስጥ የሚኖር ዘላለማዊ እውነት መሆኑን በማመን ክርስቲያኖች ሁሉ በየዓመቱ ያከብሩታል።

በጥበቡ አስፋው