Search

የኢትዮጵያ ገና ከአውሮፓውያኑ የልደት በዓል ቀን ለምን ተለየ? ከኢትዮጵያ ጋር ገናን የሚያከብሩ

ረቡዕ ታኅሣሥ 29, 2018 3702

በኢትዮጵያ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 ቀን ይከበራል፤ የጳጉሜን ወር 6 ቀናት ስትሆን ደግሞ በቀጣዩ ዓመት ገና ታኅሣሥ 28 ቀን ሆኖ በታላቅ መንፈሳዊ እና ባህላዊ ክዋኔዎች ይከበራል።

ይህ በዓል ከምዕራባውያን የልደት በዓል (ዲሴምበር 25) ጋር ለምን የቀን ልዩነት እንደኖረው እና የኢትዮጵያ አቆጣጠር ምን እንደሚመስል የቱሪዝም ባለሙያዎች እና የሃይማኖት ሊቃውንት የሚከተለውን ማብራሪያ ይሰጣሉ።

የልደት በዓል የቀን ልዩነት የመጣው ኢትዮጵያ ቀን ስለቀየረች ሳይሆን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቀን አቆጣጠር ለውጥ ስላደረገ መሆኑ በስፋት ይገለጻል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ10 በላይ ሀገራት በዓሉን ከኢትዮጵያውያን እኩል ታኅሣሥ 29 ያከብሩታል። 

ለመሆኑ የኢትዮጵያ ገና ከአውሮፓውያኑ የልደት በዓል ቀን ለምን ተለየ?

የጎርጎርዮሳዊ ካላንደር ለውጥ (በ1582) 

እስከ 1582 ድረስ መላው የክርስትና ዓለም የሚከተለው የጁሊያን (Julian) አቆጣጠርን ነበር። በኋላ ላይ ግን የሮማው ሊቀ ጳጳስ ግሬጎሪ 13ኛ የፀሐይ መግቢያ እና መውጫን ተንተርሰው የቀን አቆጣጠር ማሻሻያ አደረጉ። 

በዚህ ወቅት የግሪጎራውያኑ ካላንደር የራሷ የ13 ወራት ካላንደር ካላት ኢትዮጵያ ጋር የ7 እና የ8 ዓመታት እንዲሁም በየወራቱ የቀናት ልዩነቱ መፈጠሩን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ አቆጣጠር እያንዳንዳቸው 30 ቀናት እና የጳጉሜ ወር 5 ወይም 6 ቀናትን ያያዘች በመሆኑ፣ የዘመን ስሌቱን ወጥ እና ሳይዛባ እንዲቀጥል አድርጎታል። በዚህም በኢትዮጵያ የገና በዓል ታኅሣሥ 29 ቀን (ጳጉሜን ስድስት ስትሆን ደግሞ ታኅሣሥ 28) ሲከበር ቆይቷል።

የተመራማሪዎች ምልከታ

በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩ ታዋቂ የሳይንስ እና የሥነ-ከዋክብት ታሪክ ተመራማሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት የኦስትሪያ እና አሜሪካ ጥምር ዜግነት የነበራቸው ኦቶ ኑገባወር፣ "Ethiopic Astronomy and Computus" በሚለው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያን የዘመን ቀመር በዝርዝር አቅርበዋል።

ተመራማሪው ኢትዮጵያ ያንን ጥንታዊ እና ሳይንሳዊ የዘመን ቀመሯን ሳትለውጥ በማስቀጠሏ ከአውሮፓውያን ዘመን ጋር ሊለያይ መቻሉን አስረድተዋል።

ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የጥንታዊ መጻሕፍት እና የታሪክ ተመራማሪ ጌታቸው ኃይሌ (ፕ/ር) ስለ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር እና ስለ ልደት በዓል አቆጣጠር በሰፊው ጽፈዋል።

ፕሮፌሰሩ እንደሚገልጹት፣ በዓለም ላይ ሁለት ትልልቅ የዘመን ስሌቶች አሉ። አንደኛው "ዲዮናስዮስ ኤክሲጉስ" የተባለው መነኩሴ ክርስቶስ የተወለደበትን ዓመት ሲያሰላ የፈጠረው ስህተት ሲሆን፣ ይህም የምዕራባውያኑን ዓመተ ምሕረት ከኢትዮጵያ በ7 ወይም 8 ዓመት እንዲያንስ አድርጎታል። 

ሁለተኛው ደግሞ በ1582 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ግሬጎሪ 13ኛ የወራትን እና የቀናትን ስሌት ሲያስተካክሉ ቀናትን በመቀነሳቸው የመጣ ልዩነት ነው። 

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኢትዮጵያ የፀናችው በቀደመው እና በማይለወጠው ቀመር ላይ ነው በማለት ምዕራባውያኑ የቀን ለውጥ የተከሰተበትን አግባብ በታሪካዊ ሰነዶች አስረድተዋል።

ባሕረ  ሐሳብ

አቡ ሻከር የተባለው እና በ13ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ሊቅ የጻፈው እና በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ እንደ ማጣቀሻ የሚወሰደው የባሕረ ሐሳብ መጽሐፍ ለዚህ ጥያቄ ትልቅ ምላሽ ይሰጣል።

ይህ መጽሐፍ በሃይማኖታዊስ ዕሳቤ መሠረት ዓለም ከተፈጠረበት 5 ሺ 500 ዓመተ ዓለም ጀምሮ የፀሐይ እና የጨረቃን ዑደት መሠረት በማድረግ በዓላት በየትኛው ቀን መዋል እንዳለባቸው በዝርዝር ያስቀምጣል። 

በዚሁ ቀመር መሠረት ታኅሣሥ 29 ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን ሆኖ ተቀምጧል። ይህ መጽሐፍ አውሮፓውያን አቆጣጠራቸውን ከመቀየራቸው በፊት የነበረውን ጥንታዊ የዘመን ስሌት የያዘ ነው። 

 

በጌትነት ተስፋማርያም