Search

ከትንቢት እስከ በረት፤ የክርስቶስ መወለድ እና ምስጢሮቹ

ረቡዕ ታኅሣሥ 29, 2018 117

ኢየሱስ ክርስቶስ በሌሊት የተወለደው በኃጢአት ጨለማ ውስጥ ለነበረው ዓለም ብርሃን ሆኖ መምጣቱን ለማብሰር እንደሆነ ክርስቲያኖች ሁሉ ያምናሉ።
ሌሊቱ አልፎ ቀኑ እንደሚተካ ሁሉ፣ የጨለማው የዲያብሎስ አገዛዝ አብቅቶ የጽድቅ ፀሐይ መውጣቱን በምስጢር ያሳያል ብለውም ያስባሉ።
ንጉሥ ሆኖ ሳለ በበረት መገኘቱ፣ ለደካሞችና ለተናቁት ቅርብ መሆኑን እንዲሁም ቁሳዊ ሀብት ሳይሆን መንፈሳዊ ትሕትና ለድኅነት አስፈላጊ መሆኑን ለማመላከት ልደቱ ባልተጠበቀ ሥፍራ የመሆኑ ማሳያም ተደርጎ ይታሰባል። ይህም የሰው ልጅን ትሕትና ለማስተማርና የሰውን ልጅ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ እንደሆነ በማሰብ ዛሬም ምዕመናን ይህን ይጠብቁታል።
የክርስቶስ ልደት በምክንያትና በምስጢር የተከበበ፤ ለዘመናትም ሲጠበቅ የነበረ በመሆኑ፣ እያንዳንዱ ክስተት ለሰው ልጅ ድኅነት ያለውን ፋይዳ ይገልጻል። ጥቂቶችን እንመልከታቸው፦
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ክርስቶስ በቤተልሔም የተወለደው ነቢያት ቀድመው የተነበዩትን ትንቢት ለመፈጸም ሲሆን፣ የቤተልሔም ትርጉም "የእንጀራ ቤት" በመሆኑ የሕይወት እንጀራ መሆኑን ለማሳየት ነው።
ቤተልሔም የንጉሥ ዳዊት ከተማ መሆኗ ደግሞ እርሱም ከዳዊት ዘር የሚወጣው እውነተኛው መሲሕ መሆኑን ለሰው ልጆች ማረጋገጫ ሆኗል።
ክርስቶስ በተወለደበት ወቅት የሕዝብ ቆጠራ የሚካሄድበት ወቅት መሆኑ ደግሞ ጌታ የዓለም ሁሉ ፈጣሪ ቢሆንም ለሥጋዊ ሥርዓትና ሕግ መገዛቱን ያሳያል።
በተጨማሪም ስሙ በምድራዊ መዝገብ እንዲጻፍ በማድረግ፣ የሰው ልጆች ስም በሰማያዊው የሕይወት መዝገብ እንዲሰፍር መንገዱን የከፈተበት ጥልቅ ምስጢር መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያስተምራሉ።
ከቤተልሔም እስከ በረቱ፣ ከሌሊቱ ድባብ እስከ ህዝብ ቆጠራው ድረስ ያሉት ሁኔታዎች ድንገተኛ ክስተቶች ተደርገው አይወሰዱም ይልቁንም ምልክቶች እና የእግዚአብሔርን ትሕትናና ፍቅር የሚያሳዩ ናቸው።
እነዚህ ሁኔታዎች ጌታ ሰውን ለማዳን ዝቅ ብሎ መምጣቱንና በምድር ላይ ያለውን ሥርዓት ሳይንቅ ለሰው ልጆች አርአያ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
ይህም ልደት ለሰው ልጅ አዲስ ተስፋንና የዘለዓለም ሕይወትን ይዞ የመጣ ታላቅ የደስታ ምስራች እንደመሆኑ የሰው ልጆች ሁሉ በምድራዊ የመንፈሳዊ ህይወታቸው ተስፋም ስንቅም ያደርጉታል።

 

በጥበቡ አስፋው