Search

ከትላንት ክፉ ታሪክ ይልቅ መጪው ተስፋ የገዘፈበት የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት

ረቡዕ ታኅሣሥ 29, 2018 163

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በተለያዩ ጊዜያት ለልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ አፅንኦት ከሚሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል እርቅ እና አንድነት ይገኛሉ።

በክርስቲያኖች ዘንድ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የዕርቅ መጀመሪያ ተደርጎ እንደሚታሰብ የሚጠቅሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከልደቱ በፊት በፈጣሪ እና በፍጡር፣ በሰማይ እና በምድር፣ በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል ታላቅ የጠብ ግድግዳ ተገንብቶ ለብዙ ዘመናት መቆየቱን ያወሳሉ።

የክርስቶስ ልደት እግዚአብሔር ለአዳም፣ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁየሚለው የፈጣሪ ቃል በተግባር መፈጸም የጀመረበት፤ በአምላክ እና በሰው ልጆች መካከል ዕርቅ የተወጠነባት ዕለት መሆኗንም ይጠቅሳሉ።

በዓሉ መለያየት የጠፋበት፣ ኅብረት እና አንድነት የፀናበት፣ መለኮት እና ሥጋ፣ ሕያው እና ሟች፣ ዘላለማዊ እና ጊዜያዊ፣ ፈጣሪ እና ፍጡር፣ ሰማያዊ እና ምድራዊ፣ ምሉዕ እና ውሱን፣ በተዋሕዶ አንድ ሆነው አዲስ የምሥራች የተበሰረበት እንደሆነም ነው የሚገልጹት።

የክርስቶስ ልደት የፍዳ ዘመንን ሽሮ የምሕረት ዘምንን አምጥቷል። እረኞችን ከሜዳ፣ ሰብአ ሰገልን ከሩቅ ምሥራቅ፣ ሰዎችን ከምድር፣ መላእክትን ከሰማይ ጠርቶ በአንድነት አንዲዘምሩ አድርጓል።

እነዚህን ተራርቀው የነበሩትን አሰባስቦ በአንድነት እንዲዘምሩ ያደረጋቸው ጉዳይ ከትናንት ክፉ ታሪካቸው ይልቅ የነገ የጋራ ተስፋቸው ብሩህ ሆኖ ስለታያቸው ነው።

እረኞች እና ሰብአ ሰገል፣ ሰዎች እና መላዕክት ባለፈ ታሪካቸው ከሚገናኙበት መንገድ ይልቅ ከልደቱ በኋላ በአንድነት የሚሠሩት፣ በጋራ የሚኖሩት፣ በአንድ የሚወርሱት እና በሙላት የሚኖሩበት ዘመን የተስፋ ነው።

የሰው ልጆች ዛሬ የሁሉንም ታሪክ ከክርስቶስ ልደት ጋር አስተሣሥረው የሚተርኩት "ማን ነበርክ? ከሚለው ይልቅ ማን ለመሆን ትፈልጋለህ? የሚለው የአንድነታቸው መሠረት በመሆኑ ነው" ይላሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

"የነገውን በጋራ ከተጋሩት የትናንቱን በመተሳሰብ መቀበል አይቸግራቸውም" የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በነገው ላይ ከተግባቡ በትናንቱ ላይ መስማማት እንደማይፈትናቸው የልደቱን አብነት ጠቅሰው ያስረዳሉ።

በልደቱ ትላንት ከዛሬ ጋር እንዴት እንደታረቀም፣ "እንዴት ያኛው የጥንቱ የብሉይ፣ ይሄኛው ደግሞ አዲሱ የሐዲስ ኪዳን እና ታሪክ ሆነ። የጥንቱ በአዲሱ ምክንያት ታወቀ፤ የቀድሞው በአሁኑ ምክንያት ከበረ፤ የትናንቱ በዛሬው ምክንያት ታደሰ" በማለት አሳይተዋል።

የሰው ልጅ ትዕዛዝን ሲያፈርስ እና ከእግዚአብሔር ጋር ሲለያይ ልዩነቱ ከመለያየት አልፎ ወደ ጠላትነት በመሻገር አዳምን ከገነት በማፈናቀሉ፤ አቤልን በቃየል በማስገደሉ፣ በምድር እሾህ እና አሜከላ በማብቀሉ፣ የጥፋት ውኃን እልቂት በማስከተሉ፣ ጦርነት እና ግጭትን በማትረፉ የተጠቀመው ጠላት ብቻ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።

መለያየትን አስወግዶ አንድነትን ለማምጣት ከቤተልሔም እስከ ቀራኒዮ፤ ከልደት እስከ ስቅለት፤ ከበረት እስከ ዕርገት የዘለቀ መሥዋዕትነት መጠየቁም ተጠቅሷል። የክርስቶስ ልደት ግን አንድነቱን ከማምጣት ባለፈም ጠላትነትን አስወግዶ ፍቅርን አስፍኗል፤ ውርደትንም አስወግዷል።

"ኢትዮጵያውያን የነገዋን ኢትዮጵያ የተሻለች ለማድረግ ከዚህ የልደት ታሪክ ብዙ ትምህርት ብንወስድ ይጠቅመናል" የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በየቦታው የሚታየው መለያየት እና መጠፋፋት አባዜን ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሚታየው መለያየት የተዘራብን ክፉ ዘር ውጤት በመሆኑ ጠላቶች የዘሩብን የከፋት ዘር አስወግደን አንደነታችንን እንድናጠናክር በመልዕከቶቻቸው አንስተዋል።

ለዘመናት ሲያቆጠቁጥ ከርሞ ፍሬ ያፈራውን የመለያየት ግንብ የሚፈርሰው ኢትዮጵያውን አዲስ የጋራ ታሪክ ሲሠሩ እንደሆንም አሳስበዋል።

አዲስ መንገድ ስንጀምር የትናንቱ መንገድ ሊያጣላን እንደማይገባ፣ አዲስ ዘመን ስንወጥን ያለፈው ዘመን ሊያለያየን እንደማይገባ፣ አዲስ ዓላማ አንግበን ስንነሣ የትናንቱ ዓላማ ሊያጨቃጭቀን እንደማይገባ ጠቅሰዋል።

"የጠላታችን ዓላማ አንዳችንን ጠቅሞ ሌላችንን መጉዳት ሳይሆን ሁላችንንም ማጥፋት ነው" የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) "ዲያብሎስ አዳም እና ሔዋንን አካስሶ ከፈጣሪ እንዳጣላቸው ጠላታችን አንዱን ሕዝብ ከሌላው በማጋጨት አይቆምም፤ አንዱንም ሕዝብ እርስ በርሱም ያባላዋል። ክልልን ከክልል፣ ዞንን ከዞን፣ ወረዳን ከወረዳ፣ ጎጥን ከጎጥ፣ ቤተሰብን ከቤተሰብ፣ ባልን ከሚስት፣ ልጆችን ከወላጆች እያባላ ዓለምን ሁሉ የግጭት እና የጠብ ዐውድማ ማድረግ  ምኞቱ ነው" ይላሉ።

ስለዚህ ቆም ብለን እናስብ። መንገዱ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የሚበጅ፣ ለሁላችንም በቅቶ የሚተርፍ፣ አዲስ ማንነትን ይዘን እንደገና መወለድ እንደሚያስፈልግ በመልዕከቶቻቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያውያን ከክርስቶስ ልደት መማር ያለባቸው እንደ ሰብአ ሰገል ታሪክ ሠሪ፣ እንደ ቅዱሳን መላዕክቱ ለአዲስ ታሪክ አዲስ የምሥራች አብሳሪ መሆንን እንደሆነ ነው የሚያሳስቡት።

ኢትዮጵያውያን በዚህ መንገድ ከተጓዙ በትላንት ከመጣላት ለሚበልጠው የነገ ታሪክ እንደሚነሣሡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይገልጻሉ።

በዘንድሮው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓልም ባስተላለፉት መልዕክት፣እኛ ዛሬ የቆምነው በትናንት እና በነገ መካከል ነው። ትናንትን በዛሬ ሥራችን ዋጋ እንዲያገኝ እናደርገዋለን። ነገን ደግሞ በዛሬው ሥራችን አሣምረን እንገነባዋለን። የክርስቶስን የልደት በዓል ይሄንን ታሪካዊ ኃላፊነታችንን እያሰብን እናከብረዋለን።ሲሉ ነው ነገ በእኛ ብርቱ ሥራ እንደሚገነባ ያመላከቱት።

በለሚ ታደሰ

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #Christmas #Genna #holidays