የመደመር መንግሥት በገጠርም ሆነ በከተማ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግርን ለመፍታት አበክሮ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክረምት በጎ አድራጎት መርሐ-ግብርን ወደ ላቀ ከፍታ ያሸጋገረውን የቱሉ አራራ የተቀናጀ ሞዴል መንደርን በዛሬው ዕለት መርቀዋል።
በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ “የመደመር መንግሥት ሀገራችንን ለመለወጥ፣ ለማልማት፣ ለማሳደግ እና ብልጽግናዋን እውን ለማድረግ ያለውን ራዕይ ለማሳካት ከሚያጋጥሙት ውስንነቶች አንዱ እና የመጀመሪያው የመኖሪያ ቤት እጥረት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
በከተማም ሆነ በገጠሩ የሀገራችን ክፍሎች የመኖሪያ ቤት እጥረት እንዳለ እና ያለውም ቢሆን የውኃ አቅርቦት፣ የመብራት እና የመፀዳጃ ቤት እጥረት ያለበት በመሆኑ ስታንዳርዱን ያልጠበቀ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ በበርካታ ከተሞች የኮሪደር ልማት መጀመሩን ጠቁመው፣ በዚህም ከተሞቹ እየተለወጡ ስለመምጣታቸው አንሥተዋል።
አሁንም ቢሆን ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ሆኖም በሀገር ደረጃ ከወትሮው የተሻለ ነገር መታየት ጀምሯል ብለዋል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚኖረው በገጠር በመሆኑ ገጠርን የማሻገር ሥራ መሠራቱን እና በዚህም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ሞዴል መንደሮች እየተገነቡ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ባለሃብቶች እና ግለሰቦች በተቀናጀ መንገድ ከእነዚህ ሞዴል መንደሮች ልምድ እየቀሰሙ ለኑሮ ምቹ የሆኑ፣ በሶላር የመብራት ኃይል የሚያገኙ፣ ሰዎች እና እንስሳት ለየብቻ የሚኖሩበት እና መፀዳጃ ቤት ያለው መኖሪያ ሲገነቡ የልጆቻችን ጤንነት እየተጠበቀ ከ10 እና ከ15 ዓመታት በኋላ የሕዝባችን ኑሮ እየተሻሻለ ይሄዳል፤ ራዕያችንም እውን ይሆናል ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት ሥራዎችን እየሠራ ያለው በዚህ እሳቤ እንደሆነም ነው የጠቆሙት።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ የቱሉ አራራ የተቀናጀ ሞዴል መንደርን እውን በማድረግ ረገድ በቅርበት ተከታትለው በመሥራታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበውላቸዋል።
የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም መንግሥት ኮሚመድበው በጀት ውጭ ከተለያዩ አካላት ገንዘብ በማሰባሰብ ለሕዝባቸው የተሻለ ነገር በመሥራታቸውም አመስግነዋል።
የመንግሥት ሥልጣን የያዘ እና ከሕዝብ ኃላፊነት የተቀበለ አካል መሬት በመሸጥ እና በሙስና ሕዝቡን ማማረር ሳይሆን የተሰጠውን ዕድል ተጠቅሞ ገንዘብ አሰባስቦ አቅም ላነሣቸው የኅብረተሰባችን ክፍሎች ቤት መሥራት መለመድ ያለበት ሥራ መሆኑንም ገልጸዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጻ፣ ይህ ተግባር በፖለቲካውም፣ በሞራልም፣ በሃይማኖትም ሥልጣን ላይ ካለ ሁሉም ሰው የሚጠበቅ ተግባር ነው።
“ሥልጣን ለተወሰነ ጊዜ የሚሰጥ እና የሚወሰድ በመሆኑ ሥልጣኑ የተወሰደብን ቀን ከመቆጨት በሥልጣን ዘመናችን እንደየአቅማችን የአምስትም፣ የዐሥርም ሰዎችን ሕይወት በመለወጥ ሕዝባችንን አስደስተን፣ ለራሳችንም ተደስተን፣ ሕዝባችንን ከችግር ወጥተን በምርቃት እንዲሸኘን ማድረግ መቻል ታላቅ ዕድል ነው” ሲሉ ነው የገለጹት።
ከወረዳ አመራር ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ይህንን ሁልጊዜ በልቦናቸው ማሳደር እና በዚሁ አግባብ መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
“እጅ እና ልባችንን ንፁህ አድርገን ስንሠራ እንደዚህ ዓይነት መልካም ነገር ለሕዝባችን እናበረክታለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ “ከሕዝባችን መስረቅ ስንጀምርን ግን እየተጠላላን፣ አንዳችን ሌላችንን እያስለቀስን፣ እርስ በርስ በመጠላለፍ አንድነታችንን እንንዳለን፤ እንደ ሀገርም ልናተርፍ ከምንችለው በተቃራኒው ወደ ኋላ እየቀረን ስለምንሄድ ዕድሉን አግኝታችሁ ሥልጣን ላይ ያላችሁ ሰዎች ሁልጊዜ ማሰብ ያለባችሁ ይህንን ነው” ሲሉ መክረዋል።
ሕዝቡም መረዳት ያለበት እንደ ኢትዮጵያ ያለ ግዙፍ ሀገርን በአንድ እና በሁለት ዓመት መቀየር አስቸጋሪ ስለሆነ ፍላጎት ቢኖርም ያለን ኃይል በቂ ባለመሆኑ በአንድነት እና በመደመር መንፈስ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ሐሳብ ያለው በሐሳቡ በአብሮነት መቆም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ያንን ካደረግን በሂደት የሕዝባችንን ኑሮ በመለወጥ በደስታ የተሞላ፣ ንፁህ ቦታ ላይ ውሎ ማደር የሚችል ሕዝብ ማየት እንችላለን ነው ያሉት።
ያንን እውን ለማድረግ አንድነታችንን እና ሰላማችንን መጠበቅ፣ በምንችለው ነገር መተጋገዝ እና በጋራ መቆም፤ ከዚህ በፊት የምንታወቅበትን የአብሮነት ባህላችንን ማፅናት አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዮናስ በድሉ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #PMAbiy