አንድ ሀገር የነገ ተስፋውን የሚወስነው ትውልድ ላይ በሚሠራቸው ሥራዎች ነው፡፡ የሀገር ተረካቢ ትውልድ በአካል እና በአእምሮ ታንጾ ካደገ ሀገር ወደ ተሻለ ደረጃ ታድጋለች፡፡ ትውልድ መሰረት ከሚይዝባቸው የዕድሜ ክልሎች መካከል ደግሞ ቀዳማይ ልጅነት ወሳኝ ነው፡፡
በተመድ የትምህርት፣ ሳይንስ እና የባህል ድርጅት ብያኔ መሰረት ቅድመ ልጅነት ከትውልድ እስከ ስምንት ዓመት ድረስ ያለው ዕድሜ ነው፡፡
ይህ ወቅት በልጆች ላይ ጉልህ የሆነ የአዕምሮ እድገት ጊዜ የሚካሄድበት ስለሆነ በጥንቃቄ መያዝ ያለበት መሆኑን ነው ሳይንሳዊ ጥናቶች የሚያመላክቱት፡፡

ጥራት ያለው የቀዳማይ ልጅነት አያያዝ ለጥሩ አካላዊ-አዕምሮአዊ ዕድገት፣ ለጠንካራ ማኅበራዊ-መስተጋብር እና ለቀጣይ ዘመን ምርታማነት መሰረት የሚጣልበት ጊዜ ነው፡፡
በዚህ ምክንያትም የህጻናት ጤናማ አኗኗር፣ አመጋገብ፣ ትምሀርት እና ቤተሰባዊ ግንኙነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል።
የቀዳማይ ልጅነት አያያዝን የተመለከተ የትኛውም ዓለም አቀፍ ማዕቀፍ አለመኖሩ ከተመድ ልማት ግቦች መካከል የሆነው ፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነትን የሚመለከተው ግብ አራት (SDG 4) በሚጠበቀው ደረጃ አለመሄዱ ተመላክቷል፡፡
በ2022 በኡዝቤክስታኗ ታሽኬንት የተሰበሰቡት የዩኔስኮ አባል ሀገራት ከጠቅላላው የትምህርት ወጪያቸው ቢያንስ 10 በመቶውን ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ለማዋል ቃል ገብተዋል፡፡

ሀገራት የትምህርት ውጤታቸው የተሻለ እንዲሆን ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ወቅት ማንበብና መጻፍ፣ የሒሳብ እንዲሁም የማኅበራዊ-መስተጋብር ክህሎቶች ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው ዩኔስኮ ምክረ ሀሳብ አስቀምጧል።
ቀዳማይ ልጅነት በኢትዮጵያ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህፃናት በአካል፣ አዕምሮና ሥነ-ልቦና ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ የሚያስችል ይፋ የቀዳማይ ልጅነት እንክብካቤ ፕሮጀክትን ቀርጾ ወደ ሥራ የገባው በ2013 ዓ.ም ነው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ከፅንስ እስከ ስድስት ዓመት ዕድሜ ያሉ ሕጻናት በአዕምሮ እና በአካል እንዲበለጽጉ የማድረግ ዓላማን አንግቦ እየሠራ ሲሆን፣ እናቶች፣ አሳዳጊዎች እና ባለድርሻ አካላት በሕጻናት አስተዳደግ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እያደረገ ነው፡፡

ህፃናት በመኖሪያ ቤታቸው እና በትምህርት ገበታ ላይ እያሉ ልዩ ድጋፍና ክብካቤ ማድረግን ጨምሮ የቀዳማይ ልጅነት ክብካቤ ማዕከላትን ማስፋፋት፣ የአሳዳጊዎች ሥልጠና፤ የጤና አገልግሎት እና ማኅበራዊ ድጋፍ ፕሮጀክቱ በትኩረት እየሠራባቸው ያሉ ናቸው።
በ2002 ዓ.ም የጤና ሚኒስቴር፤ የትምህርት ሚኒስቴር፤ ሴቶችና ህፃናት ሚኒስቴርና ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ በመሆን የቀዳማይ ልጅነት እድገት ፖሊሲም የባለድርሻ አካላትን ሀሳብ አካትቶ ተሻሽሎ ወደ ሥራ ገብቷል።
ከተማ አስተዳደሩ ከህጻናት እንክብካቤ በተጨማሪ ዘላቂ የህጻናት ማዘውተሪያዎችን በማዘጋጀት የትውልዱን አዕምሮ የመገንባት ሥራዎችን አየሠራ ይገኛል፡፡
በኮሪደር ልማት ውስጥ የተካተቱት የህጻናት መጫዎቻዎች እና ማዘውተሪያዎች ልጆች አካላቸውን እና አዕምሮአቸውን የሚያዳብሩባቸው ቦታዎች እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
የሥራ ቦታ የሕፃናት ማቆያ ማዕከላት፣ ማኅረሰብ አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት እድገት ማዕከላት፣ ሙሉ ወጪው በመንግሥት የሚሸፈን የሕፃናት ማቆያ ማዕከላት አና እናቶች የቀን ማቆያ ማዕከል አገልግሎቶች ላይ ትኩረት አድጎ እየሠራ ይገኛል።
የአዲስ አበባ በቀዳማይ የልጅነት ልማት ፕሮግራም ትግበራ ባስመዘገበችው ለውጥ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሞክሮ ማዕከል እሆነች ሲሆን፣ ክልሎችም አዲስ አበባ ተሞክረው ወስደው ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል፡፡
በለሚ ታደሰ