የኢትዮ-ቻይና የንግድ ልውውጡ ከ13 ቢሊዮን ዶላር በልጧል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትብብር ቀጣይነት ባለው መልኩ እያደገ በመምጣቱ በሁለቱ ሀገራት ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰትን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስፋፋ ማድረጉን አመላክቷል፡፡
በዚህም የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጡ ከ13 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የበለጠ ሲሆን፣ ይህም ቻይና ኢትዮጵያን ዋንኛ የንግድ አጋር በማድረግ ግንኙነቷን እያጠናከረች መሆኑን ማሳያ ነው ብሏል፡፡
ኢትዮጵያም ከቻይና የምታስገባው ምርት በተጠናቀቀው ዓመት መጀመሪያ ላይ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን በመጋቢት ወር ብቻ 1.57 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ደርሷል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 22 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ሲል አገልግሎቱ ገልጿል።
የውጭ ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰትም ጠንካራ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን፣ ቻይና በማኑፋክቸሪንግ፣ በመንገድና ሕንጻ ፕሮጀክት ግንባታዎች ላይ በመሰማራት ግንባር ቀደም ሀገር ሆና እየሰራች መሆኗንም አመላክቷል።
የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞን የሚያፋጥኑ የመሠረተ ልማትና የፋይናንስ ተደራሽነት ማስፋፋት በተለይ ከባቡር ሐዲድ ዝርጋታ፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች እስከ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ድረስ የተገኙ ስኬቶች የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ አጋርነትን ማጠናከሩን አስታውቋል።
የኢኮኖሚ ትብብሩ የአጋርነቱ የጀርባ አጥንት ሲሆን፣ በየካቲት 2017 በአዲስ አበባ የተካሄደው የኢትዮ-ቻይና የኢኮኖሚ እና የንግድ ልውውጥ መድረክ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ እና በአቅርቦት ሰንሰለቶች ላይ ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጓል ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በዚሁ ዓመት ወደ አዲሱ የዓለም የኢኮኖሚ ጥምረት፣ BRICS+ መቀላቀሏ ለዘመናዊነት እና የቻይናን ጨምሮ ለዓለም አቀፍ ገበያዎች ተደራሽ የመሆን እድሎችን አስፍቷል ሲል አገልግሎቱ ገልጿል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የሁለትዮሽ ኢኮኖሚ አጋርነት ለሁለቱም ሀገራት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡ የኢትዮጵያን የዲጂታል ራዕይ ወሳኝ የሆኑ የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ እና የገበያዎች መዳረሻ እንድትሆን እድል የሚያሰፋ መሆኑንም አንስቷል።
ለቻይና ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ እንደ መግቢያ በር ሆና እንደምታገለግል መግለጫው አመላክቶ፤ በተለይ ከቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ጋር በማጣጣም የቻይና የረጅም ጊዜ የጋራ ልማት ራዕይን እውን ያደርጋል ብሏል፡፡
ከዚህ አንጻር የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፣ የፈረንጆቹን የ2026 አዲሱን ዓመት የውጭ አገር ጉብኝታቸውን በአፍሪካ ለመጀመር ዛሬ አዲስ አበባ መግባታቸውንም አስታውሷል።
ይህ ጉብኝት ቻይና የዓመቱን የመጀመሪያ የዲፕሎማሲ ጉዞ በአፍሪካ ሀገራት የመጀመር የ36 ዓመታት ረጅም ታሪክ አካል መሆኑንም አገልግሎቱ ገልጿል።
ጉብኝቱ በተለይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶማሊያ፣ ታንዛኒያ እና ሌሶቶን የሚያካትት ሲሆን ይህም ቻይና ለአፍሪካ ቀንድና ለቀሪው የአፍሪካ አገራት የምትሰጠውን ትኩረት ከማመላከት ባሻገር የኢትዮጵያ-ቻይና ግንኙነት ለአፍሪካ-እስያ ትብብር የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ እንዲቀጥል የጎላ ድርሻ እንዳለውም አብራርቷል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በዛሬው ዕለት በኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ መሠረተ ልማት፣ የኃይል አቅርቦት እና ትራንስፖርት ብሎም አዲስ በመፈጠር ላይ ባሉ እንደ ኢ-ኮሜርስ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና አረንጓዴ ኃይል ልማት ላይ ትብብራችንን ለማጠናከር መወያየታቸውም ተመላክቷል።
በአጠቃላይ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጉብኝት፣ በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ስልታዊ የኢኮኖሚ ትብብር አጋርነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረውና በቤጂንግ በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም (FOCAC) የተመዘገቡ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር ፋይዳው የጎላ እንደሆነ አገልግሎቱ አመላክቷል።