ፊንላንድ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ባደረገችው ጥረት ከአውሮፓውያኑ 2024 እስከ 2025 ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ዋና ከተማዋ ሄልሲንኪ አንድም የሞት አደጋ ያልተከሰተባት ከተማ ሆናለች።
ከተማዋ ይህንን ታላቅ ስኬት ማስመዝገብ የቻለችው የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ መንግሥት ባወጣው የአስር ዓመት ስትራቴጂ መሰረት የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በመገንባታቸው ጭምር መሆኑ ተገልጿል።
በዚህ ስትራቴጂ መሰረት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የብስክሌት መንገዶች ተለይተዋል፣ የመንገድ መሰረተ ልማቶች፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ የመንገድ ላይ ካሜራዎችና መሰል የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያግዙ ልማቶች ተከናውነዋል።
እንዲሁም የመኖሪያ አካባቢዎችና ትምህርት ቤቶች የሚገኙባቸው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የከተማዋ መንገዶች ላይ የፍጥነት ወሰኑ ቀድሞ ከነበረው 50 ኪ.ሜትር ዝቅ በማድረግ በሰዓት 30 ኪ.ሜትር እንዲሆን በመደረጉ ይህ ውጤት ሊመዘገብ እንደቻለ ታውቋል።
በመሆኑም በአጠቃላይ 1.5 ሚሊየን ህዝብ በሚኖርባት ዘመናዊና ትልቅ ከተማ የትራፊክ አደጋን ዜሮ በሚባል ደረጃ መቀነስ የቻለችው ሄልሲንኪ መጠነኛ ከሚባሉ የግጭት አደጋዎች ውጭ አንድም እግረኛ፣ ሾፌር ወይም የብስክሌት ተጠቃሚ ላይ ምንም አይነት የሞት ጉዳት አልደረሰም።
በዓመቱ በሄልሲንኪ የደረሱት መጠነኛ ጉዳት ያደረሱ ግጭቶችም ቢሆኑ ባለፉት ዓመታት እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ግን የተመዘገበው 277 ግጭት ብቻ ነው።
ዘመናዊና ብዙ ህዝብ በሚኖርባቸው ከተሞች ታሪክ ታላቅ የሚባል ስኬት ያስመዘገበችውን የዚህች ከተማን ተሞክሮ ለመቅሰም ብዙዎች እንደሞዴል እያነሷት ትገኛለች።