Search

ጥምቀት ከኢትዮጵያ ውጭ እንዴት ይከበራል? የጥምቀት ድምቀቶች

ሰኞ ጥር 11, 2018 1101

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥምቀትን የምታከብርበት ትውፊት ከሌሎቹ የክርስትና ዓለም ልዩ ያደርጋታል፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምታከብራቸው ዐበይት እና በከፍተኛ ድምቀት በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት ውስጥ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት አንዱ እና ዋናው ነው፡፡

ይህ በዓል በመላዋ ኢትዮጵያ በገጠርም ሆነ በከተማ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ከዋዜማው ጀምሮ ታቦታቱ በምስጋና ታጅበው ከመንበረ ክብራቸው በመነሳት ወደ ባሕረ ጥምቀት ወርደው ያድራሉ።

ሌሊቱን ሙሉ ከሚደረገው ማህሌታዊ ዝማሬ ባሻገር እንደየአካባቢው ባህል ደግሞ የተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች እየተከናወኑ በማግስቱ ጠዋት ዋናው ሥነ ሥርዓት ወይም ጥምቀቱ ተካሂዶ ታቦታቱን በማጀብ ወደ መንበረ ክብራቸው በመመለስ ይከበራል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ መጠመቁን ምክንያት በማድረግ የቃልኪዳኑን ታቦት በመያዝ ወደ ከተራ (ወንዝ) የምትወርድ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነች። በእርግጥ በጥንት የክርስትና ዘመን ውስጥ እንዲህ ያለው አከባበር በክርስቲያኖች ዘንድ የሚታወቅ እንደነበር የቤተክርስቲያን ተመራማሪዎች የሚጠቅሱት ቢሆንም፣ አሁን ላይ በብዙ ምክንያቶች ይህ ሥርዓት ተረስቶ ኢትዮጵያ ብቻ ጠብቃ አቆይታለች፡፡ ለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያኗን ልዩ የሚያደርጋት።

በዓሉ በክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውስ ዕለት እንደሆነ ይታመናል፡፡

በዓሉ ኤጲፋንያ በመባልም የሚታወቅ ሲሆን፣ ኤጲፋንያ ማለት በግሪክ ቃል መገለጥ፣ መታየት ማለት ነው። ይህም ክርስቶስ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ፣ አባቱ አብ ደግሞ ከሰማይ በደመና ሆኖ የምወደው ልጄ ይህን ነው በማለት የሥላሴ ሦስትነት እና አንድነት የተገለጸበት ዕለት እንደሆነ የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ ነው ይህ ምስጢር የተገለጠበት በመሆኑ ኤጲፋንያ ወይም የመገለጥ የመታየት በዓል እንደሆነ የሚገለጸው።

በኢትዮጵያ ጥር 10 ቀን ከተራ ነው፡፡ከተረማለትገደበማለት ሲሆን ወራጅ ውኃ ተገድቦ በአምሳለ ዮርዳኖስ ለጥምቀት የሚዘጋጅበት ነው፡፡ በዚያው ዕለት ታቦታት ከየደብራቸው ወጥተው ወደ ከተራ ይሄዳሉ፡፡ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጠመቁ አንድ ቀን አስቀድሞ በዋዜማው ከገሊላ መንደር መጥምቁ ዮሐንስ እያጠመቀ ወደነበረበት ማዕከላዊ ዮርዳኖስ ባሕር መሄዱን ለማሰብ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡ ታቦታቱ ወደ ከተራ (ወንዝ) የሚሄዱት ምዕመናን በዝማሬ እያጀቧቸው ነው። እዚያም በየተዘጋጀላው ድንኳን እንዲያርፉ ተደርጎ ሌሊቱን በማኅሌት እና ቅዳሴ ያሳልፋሉ።

ጥር 11 ቀን የጥምቀት ዕለት ሌሊት ቅዳሴ ተቀድሶ፣ ምእመናን እዚያው በድንኳኑ ዙሪያ አስቀድሰው ሲጨርሱ በካህናት መሪነት ሁሉም ወደከተራው ያመሩና ሕዝቡ ጸበል ይረጫል።

"ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ" (ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ) የሚለው የዕለቱ ዝማሬ በሊቃውንቱ አንደበት በያሬዳዊ ዜማ ይሰማል። ካህናት በመቋሚያ፣ በከበሮ እና በጽናፅል በሚታጀብ ኃይማኖታዊ ዝማሬ ያቀርባሉ።

በዚህ በዓል ላይ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ በቤተ ክርስቲያኗ ሥርዓት መሰረት በተመሳሳይ መንገድ የሚከበር ነው። ምእመናን ግን እንደየአካባቢያቸው ባህል እና ወግ መሰረት በዘፈን፣ በሆታ፤ እና በእልልታ ታቦታቱን አጅበው እንደያመጣጣቸው ወደየደብሮቻቸው ይመለሳሉ።

ከአዲስ አበባ ጃንሜዳ እስከ ጎንደር ፋሲል ጥምቀተ ባሕር፣ ከማይጨው እስከ ደንበል ሐይቅ ደሴት፣ ከምንጃር ኢራቡቲ እስከ ጋምቤላ ባሮ ወንዝ፣ ከአክሱም እስከ አርባምንጭ እና ላሊበላ በሁሉም ሥፍራዎች በዚሁ ዓይነት ደምቆ ይከበራል። የምእመናኑም ሆነ የካህናት እና የዲያቆናት አለባበስ ፍፁም በሚማርክ ባህላዊ አልባሳት የተዋበ በመሆኑ በዓሉ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁል ጊዜ አዲስ ነው።

በርካታ ታቦታት በአንድ ቦታ ተሰባስበው ማክበራቸው አንዱ የቆየ ትውፊት ነው፡፡ በርካታ ታቦታት በአንድ ቦታ ተሳባስበው ጥምቀት በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች ጎንደር፣ አዲስ አበባ ጃን ሜዳ፣ ምንጃር ሸንኮራ (44 ታቦታት በአንድ ቦታ የሚወጡበት) አርባ ምንጭ፣ ጋምቤላ እና ባቱ ደንበል ሐይቅ እንዲሁም ላሊበላ እና አክሱም ይገኙባቸዋል፡፡ አነዚህ አካባቢዎች ለረጅም ጊዜ የቆየውን የታቦታቱ በአንድ ቦታ ተሳበስቦ መውጣት ያስቀጠሉ አካባቢዎች በመሆናቸው የብዙ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ናቸው፡፡ በተለይ ጋምቤላ በባሮ ወንዝ ላይ እና በባቱ ደንበል ሐይቅ ላይ የሚከበረው በዓል በጣም የተለየ ድባብ አለው። በእርግጥ ብዙዎች የሚሄዱት እና የሚያውቁት የጎንደር እና አዲስ አበባ የጥምቀት በዓል እንደሆነ ሳይዘነጋ ማለት ነው። 

በሌላው የዓለም ክፍል ጥምቀት መቼ እና እንዴት ይከበራል?

በምሥራቃውያንም ሆነ በምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት በተለይም ከኦርቶዶክስ ውጭ በሆ ዘንድ ኤጲፋኒያ (ጥምቀት) የሚከበር ቢሆንም፣ በመካከላቸው ያለው ትልቅ ልዩነት በዓሉ የሚከበርባቸው ክንውኖች ናቸው።

ለምዕራባውያን ክርስቲያኖች በዓሉ በዋነኝነት የሚከበረው የክርስቶስን መወለድ ተከትሎ ወደ ቤተልሔም የመጡትን ሰብአ ሰገል ለማሰብ እና በገሊላ ቃና የሠርግ ሥነ ሥርዓት የተሰራውን የክርስቶስን ተአምራት በማሰብ ብቻ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የክርስቶስ ጥምቀትን የሚያከብሩት ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ እንደሄደው ወደ ወንዝ በመሄድ ነው። በሁለቱም ትውፊቶች የበዓሉ ፍሬ ነገር የክርስቶስ በሥጋ ለዓለም መገለጥን ነው። ክርስቶስ በይፋ ለሕዝብ የተገለጠበት ነው ተብሎ የሚታመነው በቃና ዘገሊላ ሠርግ ላይ የታየው ውኃን ወደ ወይን የመለወጥ ተአምር የሚታሰበው በዚሁ በጥምቀት ወቅት ነው።

ካቶሊክን የመሰሉ የምእራባውያን አብያተክርስቲያናት የጥምቀትን በዓል ከልደት በዓል ጋር ያከብሩ የነበረ ሲሆን፣ 1955 ጀምረው ግን ሁለቱን በመለያየት ልደትን በታኅሳስ 25 ጥምቀትን ደግሞ በጥር 6 ያከብራሉ፡፡

እንደ አንጀሊካን፣ የሉተራን እና የሜቶዲስት አብያተ ክርስቲያናት ተከታዮች ያሉ በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከታኅሣሥ 25 ጀምሮ የአሥራ ሁለት ቀን በዓል የሚያከብሩ ሲሆን፣ ጥር 5 ላይክሪስማስታይድወይምአሥራ ሁለቱ ቀናትየማጠቃለያ ዋዜማ ዝግጅት ያደርጋሉ።

ሀንጋሪያውያን ጥምቀትን ለማመልከት ጥር 6 የሚከበረውን በዓልቪዝኬሬሽት ብለው ይጠሩታል፤ ይህ ስያሜ "ቪዝ" (ውኃ) እና "ኬሬሽት፣ ኬሬሽ-ሴግ" (ጥምቀት) የሚሉትን ቃላት ያስታውሳል።

የእምነቱ ሊቃውንት የጥምቀት በዓል በምዕራቡ ዓለም መከበር የጀመረበት ሁኔታ ግልጽ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን ጥምቀት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ለምዕራባውያኑ እንዳስተዋወቁ እና አዲሱ የጥምቀት አከባበር ከልደት ተለይቶ ራሱን ችሎ እንዲከበር ተደርጎ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንም ይህንን ባህል እንዳስፋፋች ይገለጻል።

የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በዓሉን የሚያከብሩት ቴዎፋኒ በማለት ሲሆን፣ ትርጓሜውም "እግዚአብሔር አንጸባረቀ" ወይም "መለኮት ተገለጠ" ማለት ነው። ጥምቀት በምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ከፋሲካ እና ከጰራቅሊጦስ በዓል በመከተል ትልቅ በዓል በመሆኑ በድምቀት ይከበራል።

በቡልጋሪያ፣ በግሪክ እና በሩማንያ የሚገኙ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ግን ጥር 6 ቀን በዓሉን ያከብራሉ።

ነገር ግን የጁልያንን የዘመን አቆጣጠር ለሚከተሉት በሩሲያ፣ በሰርቢያ እና በዩክሬን የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ጥምቀትን የሚያከብሩት በአውሮፓውያኑ ጥር 19 ቀን ነው። ይህ ቀን ኢትዮጵያ ከምታከብርበት ጥር 11 ቀን ጋር ተመሳሳይ ዕለት ነው፡፡

ልክ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጥምቀትን የምታከብርበት ሃይማኖታዊ ትውፊት ሁሉ የኦሬንታል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች፣ የግብፅ ኮፕቲክ፣ የአርመን፣ የሶሪያ እና የህንድ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ለረጅም ዘመናት በቆየው ትውፊታቸው ወደ ወንዝ በመውረድ እና በመጠመቅ ቀኑን ያከብራሉ፡፡

በለሚ ታደሰ