Search

ከሳይንስ ልብ-ወለድ ወደ ጦር ሜዳ፦ የህንድ “አይረን ማን” እና የመከላከያ ኢንዱስትሪው ግስጋሴ

ረቡዕ ጥር 13, 2018 627

በሲኒማ ጥበብ ለም “አይረን ማን” (Iron Man) የተሰኘው የሳይንስ ልብ ወለድ ፊልም ገጸ-ባሕርይ ቶኒ ስታርክ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተገነባ ልብስ ታግዞ በሰማይ ላይ ሲምዘገዘግ ማየት ለብዙዎቻችን አስደናቂ ትዕይንት ነበር።

በተመሳሳይ በህንድ ቦሊውድ ሲኒማም በቅርቡ በታየው “ፓታህን” (Pathaan) ፊልም ላይ ሻህሩክ ካን በጀርባው ባጠለቀው የጄት መሣሪያ ታግዞ ከጠላቶቹ ጋር በአየር ላይ ሲፋለም ታይቷል።

ይህ ለአንድ መቶ ዓመታት ያህል በልብ ወለድ ድርሰቶች ውስጥ ብቻ ታጥሮ የቆየው “የሚለበስ በረራ” (Jetpack) ቴክኖሎጂ፣ ዛሬ ከፊልም ስክሪን ወጥቶ በገሃዱ ዓለም የጦር ሜዳና የነፍስ አድን ስራዎች ላይ ስምሪት መጀመሩን የህንድ መከላከያ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

የጄትፓክ (Jetpack) ቴክኖሎጂ በህንድ ወታደራዊ ልምምድ

በአየር ላይ የመንሳፈፍ እና የመብረር አቅም የሚሰጠው ይህ ልብስ፣ በፈሳሽ ጋዝ የሚንቀሳቀስና ግለሰቡን ከምድር ከ10 እስከ 15 ሜትር ከፍታ ላይ እንዲንሳፈፍ የሚያደርግ ነው።

ልብሱ በሰዓት 50 ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም ያለው ሲሆን፣ በተለይም ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ ተራራማ አካባቢዎች ፈጣን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግና የነፍስ አድን ስራዎችን ለማከናወን ታስቦ የተሰራ ነው።

እንደ ኤንዲ ቲቪ (NDTV) ዘገባ ከሆነ፣ የህንድ ጦር ሃይል “አብሶሉት ኮምፖዚት” (Absolut Composite) በተባለ ሀገር በቀል ኩባንያ የተመረቱ 48 የጄትፓክ አልባሳትን ለማዘዝ ዝግጅቱን አጠናቋል። ይህ እርምጃ ህንድ በመከላከያ ዘርፍ ያላትን የቴክኖሎጂ አቅም ከማሳየቱም በላይ፣ የወታደሮቿን ተንቀሳቃሽነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሎ ታምኖበታል።

ከገቢ አቅራቢነት ወደ ላኪነት የህንድ ግዙፍ እቅድ

ላለፉት አስር ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ የጦር መሳሪያ ገዥ ሆና የቆየችው ህንድ አሁን ግዙፍ ስትራቴጂያዊ ለውጥ እያደረገች ትገኛለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በቅርቡ እንደገለጹት፣ ሀገሪቱ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ወደ ውጭ የምትልካቸውን የመከላከያ ምርቶች በሶስት እጥፍ ለማሳደግ አቅዳለች።

•  የወጪ ንግድ ግብ፦ ህንድ በአሁኑ ወቅት ከዘርፉ የምታገኘውን 2.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ እየሰራች ነው።

•  የገበያ ስፋት፦ በአሁኑ ወቅት ኒው ዴልሂ ለ75 የዓለም ሀገራት የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መላክ ጀምራለች።

•  ተጠቃሚ ሀገራት፦ ፊሊፒንስ፣ ሞሪሸስ፣ ኢኳዶር እና ማሌዢያ ከህንድ ሄሊኮፕተሮችን፣ ክሩዝ ሚሳይሎችን እና ሌሎች ወታደራዊ መሣሪያዎችን በመግዛት ላይ ያሉ ቀዳሚ ሀገራት ናቸው።

የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ራጅ ናዝ ሲንግ እንደገለጹት፣ እንደ ህንድ ያለ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን የሚጥር ሀገር በውጭ ምርቶች ላይ ጥገኛ መሆን የለበትም። በመሆኑም መንግሥት የመከላከያ ምርምርና ልማት (R&D) ፖሊሲዎችን በማሻሻል ሀገር በቀል እውቀትን ወደ ምርት ለመቀየር ከፍተኛ በጀት መድቧል።

"የሰው ሃይልና ጊዜ ወሳኝ ናቸው"፦ ባለሙያዎች

ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ራስን የመቻል ጉዞ ቀላል እንዳልሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ጡረተኛው የአየር ሃይል አባል ኤር ማርሻል ማን ሙሃን ባሃዱር እንደሚያስገነዝቡት፣ የጦር ሃይልን ማዘመንና የራስን ኢንዱስትሪ መገንባት የሚከናወነው በሂደት ነው።

“ትልቁ እና መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ የሰለጠነ የሰው ሃይል ነው። ቴክኖሎጂውን ለመቆጣጠርና ለማልማት ጊዜ ያስፈልጋል። የሀገር ውስጥ ምርትን ከውጭ ከሚገቡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር በጥምረት በመጠቀም የራስን ኢንዱስትሪ ማብቃት የግድ ነው” ሲሉ ኤር ማርሻል ባሃዱር ምክራቸውን ይለግሳሉ።

ህንድ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የዓለም ሶስተኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ ለመሆን የያዘችውን ራዕይ ከዳር ለማድረስ፣ የመከላከያ ኢንዱስትሪውን እንደ ዋና ሞተር እየተጠቀመችበት ትገኛለች። ይህም ከሲቪል አውሮፕላኖች ምርታማነት ጀምሮ እስከ የጠፈር ቴክኖሎጂ ድረስ ያለውን ዘርፍ እንደሚያነቃቃው ይጠበቃል።

 

በሰለሞን ገዳ