እያንዳንዱ ዜጋ የማኀበረሰቡን መልካም እሴቶች በመጠበቅ የቀደመ ማንነታችን መመለስ ይኖርበታል ሲሉ ምሁራን ገለፁ፡፡
ኢቢሲ በአዲስ ቀን 'የሀገር ጉዳይ' መሰናዶ ላይ መልካም እሴቶችን በሚመከተ እንግዶች ጋብዞ ቆይታ አድርጓል፡፡
በሐዋሳ ዩንቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዳኜ ሽብሩ (ዶ/ር)፤ እሴቶቻችን የአንድ ማኀበረሰብ ባህሪ፣ ድርጊትን እና አኗኗር የሚወስኑ መርሆች ናቸው ብለዋል፡፡
የታመመን ማገዝ፣ አቅመ ደካማዎችን ማክበር፣ የታረዘን ማልበስ፣ ፣ የተራበን ማብላት፣ አሉታዊ ርምጃዎችን ማረቅ እን የተለያዩ የቀደሙ የኢትዮጵያዊያን እሴቶችን ማጠናከር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ሀገር ወዳድነት፣ ይቅርታ አድራጊነት እና ሌሎችም መልካም ምግባራት የማኀበረሰቡ እሴት መገለጫዎች ስለሆናቸው ነው ያነሱት።
እነዚህ እሴቶች ጠፍተዋል ማለት ባይቻልም እለት በእለት እየደበዘዙ መምጣታቸውን አመላክተው፤ በበርካታ ቦታዎች መደጋገፉ እና መተሳሰቡ አሁንም ቢኖርም ከባህል እና ከእሴት ያፈነገጡ ጉዳዮች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
ከተማዎች ላይ የግለኝነት ስሜት እንደሚበራከት ጠቁመው፤ መልካም እሴቶች በመጠበቅ የቀደመ ማንነታችን መመለስ ይኖርብናል ብለዋል።
በወላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ የሶሺዬሎጂ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ሙሉቀን ታምራት (ረ/ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ኩራት የሆኑ እሴቶች አሁን ባለው ትውልድ እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን ነው ያነሱት፡፡
በፊት የነበሩ የአብሮነት እና የአንድነት ሕይወት እለት በእለት እየተሸረሸረ በመሆናቸው እንደሀገር ጉዳት እንዳለው ነው የገለጹት፡፡
አሁን የመጣው የዘመናዊነት ቀመስ ሕይወት ለመልካም እሴቶቻችን መሸርሸር ምክንያት ስለመሆኑ አስረድተዋል።
እራስ ወዳድነት አሁን በስፋት እየታየ መሆኑን አንስተው፤ ቀድሞ የነበረ ባህላችንን የሚንጻረር ስለመሆኑ ነው ያስታወቁት፡፡
በሜሮን ንብረት