Search

በአፋር ክልል በመሬት መንቀጥቀጥ ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖች ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ ነው

በአፋር ክልል ከአዋሽ ፈንታሌ እና ዱል ኤላሳ ወረዳዎች በመሬት መንቀጥቀጥ ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖችን ወደ አካባቢያቸው የመመለስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገልጿል።
ህብረተሰቡን ወደ አካባቢው የመመለስ ስራ ከመጀመሩ በፊት የመሬት መንቀጥቀጡ በተከሰተበት አካባቢ ጥናት መካሄዱን እና ከተፈናቃዮች ጋር ውይይት መደረጉን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መሃመድ ሁሴን ለኢቲቪ ተናግረዋል።
ተፈናቃዮቹ ከነበሩባቸው 3 ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች በዳኢዶ እና አዲስ ራዕይ መጠለያ ጣቢያዎች የነበሩትን የመመለስ ስራ የተከናወነ ሲሆን፣ በቀጣይ ደላካራ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ያሉትን ተፈናቃዮች የመመለስ ስራ እንደሚሰራ ዋና ኮሚሽነሩ አመላክተዋል።
ከፌዴራል መንግስት፣ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች እና ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን በመሬት መንቀጥቀጡ ተጎድተው የነበሩ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት የመጠገን ሥራ ተጀምሮ እየተከናወነ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ ያሉ ተፈናቃዮች ተረጋግተው ወደ መደበኛ ኑሯቸው እኪመለሱ ለ3 ወር የሚሆን መሰረታዊ የምግብ ፍጆታ ለማቅረብ መታቀዱን ገልጸው፤ አሁን ላይ ለ1 ወር የሚሆን የመሰረታዊ ፍጆታዎች ድጋፍ እንደተደረገ ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
በሁሴን መሐመድ