Search

የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ሲጠናቀቅ የከተማዋን ኢኮኖሚና የኑሮ ደረጃ ከፍ ያደርጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ሲጠናቀቅ አካባቢያችንን ከመጠበቅ ባሻገር ለአዲስ አበባ ደማቅ እና ዘላቂ የወንዝ ዳርቻዎችን በማስገኘት የከተማዋን ኢኮኖሚ እና የኑሮ ደረጃ ከፍ ያደርጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ጋር የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት የሥራ ሂደትን ተመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን አስመልከቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት ፅሁፍ፤ ጤናማ፣ በሚገባ የተጠበቁ የወንዝ ዳርቻዎች የከባቢ ሥርዓትን እና የውሃ ጥራትን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰብን የኑሮ ደህንነት የሚያሻሽሉ እና የከተሞችን ለፈተና አለመበገር የሚያጠናክሩ ደማቅ ሕዝባዊ ሥፍራዎችን ይፈጥራሉ ብለዋል።
ይኽ ሥራ አሁን በተያዘው ምዕራፍ በአምስት ክፍለ ከተሞች የሚዘልቅና 21.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በጥቂቱ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መንገድ፣ ሕዝባዊ ፕላዛዎች፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎች፣ ሱቆች እና አምፊ ቴአትሮች የተካተቱበት እንደሆነም አንስተዋል።
ከዚህ ግዙፍ ሥራ አላማዎች መካከልም የወንዞች ብክለትን ማስወገድ፣ የከተማዋን የጎርፍ ተጋላጭነት መቀነስ፣ ሕዝባዊ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ የአረንጓዴ ስፍራዎችን ቁጥር መጨመር እና የሥራ እድል መፍጠር እንደሚገኙበትም አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አካባቢያችንን ከመጠበቅ ባሻገር ለአዲስ አበባ ደማቅ እና ዘላቂ የወንዝ ዳርቻዎችን በማስገኘት የከተማዋን ኢኮኖሚ እና የኑሮ ደረጃ ከፍ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።