የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ መጀመሩን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለፁ።
በአዉሮፓ፣ እስያ እና አፍሪካ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራው በበይነ መረብ አማካኝነት እንዲሁም አንዳንድ ሀገራት ላይ በአካል በመሄድ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
አምስት ኮሚሽነሮች የተካተቱበት ልዑክ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በአካል ተገኝቶ አጀንዳ ለመሰብሰብ ዝግጅቱን አጠናቆ ከነገ ነሀሴ 3 2017 ዓ.ም ጀምሮ ስራውን እንደሚጀመሩ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን አረአያ ከኢቲቪ 57 የአጀንዳ ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ አጀንዳ የማሰባሰቡ ስራ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ አጀንዳዎችን አንጥሮ በማውጣት ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው እንደሚያዘጋጁም ጠቅሰዋል።

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ያለ ምንም አይነት ውጫዊ እና ውስጣዊ አካል ተፅዕኖ እንደሚከናወን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ዜጎች ራሳቸዉ እንዲወስኑ መደረጋቸው እና በጋራ የሚወያዩበት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያዊያን ለእቅዱ መሳካት በጋራ መስራት እንዳለባቸው እና ጉባኤዉ በቀጣይ ዓመት እንደሚጀመርም ፕሮፌሰር መስፍን ተናግረዋል።
በቢታንያ ሲሳይ