የብሪክስ አባል አገራት በአንድ በኩል ከዋሽንግተን የሚሰነዘርባቸውን አዲስ የጂኦ-ፖለቲካዊ ጫና፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ልጅ ሕልውናን እየተፈታተነ ያለውን የአየር ንብረት መዛባት ለመመከት ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው።
የስብስቡ አባል አገራት እነዚህን ሁለት ታላላቅ ፈተናዎች ማዕከል በማድረግ የዓለምን የወደፊት አቅጣጫ ለመቀየር ግብግብ ላይ መሆናቸውን ነው መረጃዎች የሚያመላክቱ።
በአንድ በኩል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጫናን በመቋቋም በሌላ በኩል ደግሞ አማራጭ አቅጣጫዎችን በመከተል አባል ሀገራቱ እያሳዩ ያለው ትጋት ከስጋት ወደ ዕድል የሚቀየር መንገድ እንዳለ አመላካች መሆኑን ብሪክስ ቴሊቪዝን ዘግቧል።
የተባበሩት መንግሥታት "የመፍላት ዘመን" ሲል የጠራው ወቅታዊው የአየር ንብረት መዛባት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ500 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢኮኖሚ ኪሳራ እያስከተለ ነው። ቻይና፣ ብራዚል እና ሩሲያ በከባድ ጎርፍ፣ በቃጠሎ እና በበረዶ መቅለጥ አደጋዎች እየተፈተኑ ይገኛሉ።
ብሪክስ ይህንን ቀውስ ለመመከት ታዳጊ አገራት የሚያስፈልጋቸውን 1.3 ትሪሊዮን ዶላር የአየር ንብረት ፋይናንስ በፍትሐዊነት እንዲቀርብ ዓለም አቀፍ ግፊት እያደረገ ነው።
ኢትዮጵያ በብሪክስ ውስጥ ያላት ሚና በአረንጓዴ ልማት ላይ የተመሠረተ ነው። ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመተከል የተመዘገበው የ"አረንጓዴ አሻራ" ስኬት፣ ዛሬ በብሪክስ መድረክ እንደ ትልቅ የፖሊሲ ተሞክሮ እየተጠቀሰ ይገኛል።
ይህ ስኬት ለሕንድ የጽናት አጀንዳ እንደ ስኬታማ ግብዓት እያገለገለ ሲሆን፣ ለቻይና እና ለሩሲያ ደግሞ ኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይል ማዕከል አድርገው እንዲመለከቱ ዕድል ፈጥሯል።
ብሪክስ ወደ ታዳሽ ኃይል የሚደረገው ሽግግር "ፍትሐዊ" (Just Transition) መሆን እንዳለበት ያምናል። በዚህም መሠረት እንደ ሻንጋይ ያሉ ከተሞች ጎርፍን መሬት ውስጥ በመምጠጥ መልሰው ለልማት የሚጠቀሙበት "የስፖንጅ ከተማ" ጥበብ፣ በሌሎች አባል አገራትም እንዲተገበር በቴክኖሎጂ ልውውጥ እየተሠራበት ነው።
እነዚህ ጨምሮ ብሪክስ ከአዲሱ የዋሽንግተን ጫና ራሱን እየተከላከለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዓለምን ከአየር ንብረት ጥፋት ለመታደግ በተግባራዊ እርምጃዎች እየመራ እንደሚገኝ ብሪክስ ቲቪ በዘገባው አመልክቷል።
በሰለሞን ገዳ