Search

በጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት ላይ ለተሳተፉና ድንቅ ብቃት ላሳዩ አብራሪዎች እውቅና ተሰጠ

ሓሙስ ጥር 21, 2018 377

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሠረተበትን 90ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ፣ "የአንበሶቹ ሰማይ" በተሰኘው ደማቅ የአየር ትርኢት ላይ ተሳትፈው የላቀ ወታደራዊ ጥበብና ጀግንነት ላሳዩ አብራሪዎች የእውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር ተካሄደ።
በመርሐ ግብሩ ላይ፣ የሀገሪቱን ሰማይ በጥበብና በጀግንነት ላደመቁት አብራሪዎች የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የሽልማትና የእውቅና ምስክር ወረቀት አበርክተዋል።
ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ አብራሪዎቹ ያሳዩት የላቀ ጥበብ ከተራ ወታደራዊ ትርኢት ባለፈ የተቋሙን የቴክኖሎጂ የበላይነትና ሁለንተናዊ ዝግጁነት ለዓለም ያስመሰከረ መሆኑን ገልጸዋል።
"ከተቋማችን አልፎ ኢትዮጵያን አኩርታችኋል፤ የአየር ኃይልን የማድረግ አቅም በተግባር አረጋግጣችኋል" ሲሉም አብራሪዎቹን አወድሰዋል።
"የነፃነትና የአንድነት ምልክት" በሚል መሪ ቃል የተከበረው ይህ በዓል፣ አየር ኃይሉ ባለፉት ዘጠኝ አስርት ዓመታት የገነባውን ታሪክና ዘመናዊነት ያሳየበት ሆኖ አልፏል።
የተሰጠው እውቅናም አብራሪዎች ለሀገር ሉዓላዊነት ለሚያደርጉት ተጋድሎ ክብር ለመስጠ፣ ለቀጣዩ የአየር ኃይል ትውልድ የሞራል መነሳሳትን ለመፍጠር እንዲሁም የሀገርን የአየር የበላይነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።