Search

"ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የዓለምን አካሄድ የቀየረችበት ድንቅ ታሪክ ነው" - ትሬቨር ኖዋህ

ሓሙስ ጥር 21, 2018 330

ቀደም ሲል የDaily Show አሁን ደግሞ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን የሚዳስስ ፖድካስት የሚያዘጋጀው አፍሪካ አሜሪካዊው ትሬቨር ኖዋህ፣ ከባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ ጋር ልዩ ቆይታ አድርጓል።

በቆይታቸው ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያነሣው ሐሳብ እሱ ግድቡን የተረዳበት መጠን ከፍተኛ እንደሆነ አመላክቷል።

ትሬቨር ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሰጠው አድናቆት እና የውይይቱ ዋና ዋና ነጥቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል፦ 

ራስን የመቻል አብዮት

ትሬቨር በውይይቱ ላይ እጅግ ያስገረመው ነጥብ ኢትዮጵያ ግድቡን የገነባችበት መንገድ መሆኑን ገልጿል። ዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ፊታቸውን ባዞሩበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ የራሷን አቅም በመጠቀም እና እያንዳንዱ ዜጋ ካለው ላይ ቀንሶ በሰጠው መዋጮ ቢሊዮን ዶላሮችን ማሰባሰቧን "አብዮታዊ" ሲል ገልጾታል። ይህ ለሌሎች አዳጊ ሀገራት "ያለ ውጭ ብድር ታላቅ መሆን ይቻላል" የሚል ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁሟል።

[የ130] ሚሊዮን ሕዝብ ተስፋ

ትሬቨር አክሎም፣ ይህ ግድብ ለኢትዮጵያ ዝም ብሎ ግንባታ ሳይሆን፣ [ከ130] ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው ሕዝብ በተለይም ኤሌክትሪክ ለማያገኘው ከግማሽ በላይ ወገን፣ መሠረታዊ የለውጥ ምንጭ መሆኑን ገልጿል። ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግር እያደረገች ያለችው አካባቢን በማይበክል ንፁህና ታዳሽ ኃይል መሆኑም ልዩ እንደሚያደርገው አንሥቷል። 

የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓድዋ

የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ በበኩላቸው፣ በጉዳዩ ላይ ከትሬቨር ኖዋህ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ፣ ግድቡን በታሪክ ትልቅ ቦታ ካለው ከ1888ቱ የዓድዋ ድል ጋር አነፃፅረውታል።

ኢትዮጵያውያን ወራሪውን የፋሺስት ጦር ድል አድርገው ለአፍሪካ የነፃነት ፋና እንደሆኑት ሁሉ፣ ዛሬም ይህን ግዙፍ ግድብ በራሳቸው አቅም ገንብተው በማጠናቀቅ "የዘመኑን የዓድዋ ድል" አስመዝግበዋል ሲሉ ገልጸውታል።

የራስን ወንበር ይዞ መምጣት

ሁለቱም ሰዎች ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ያመጣችውን አብዮት የገለጹት፣ "ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጠረጴዛው ዙሪያ ወንበር ካልሰጠህ፣ የራስህን የሚታጠፍ ወንበር (Folding Chair) ይዘህ መምጣት አለብህ" በማለት ነው።

ኢትዮጵያ የዓለም የገንዘብ ሥርዓት ወንበር ቢነፍጋትም፣ በራሷ ጥረት የራሷን ወንበር ይዛ በዓለም መድረክ ላይ በኩራት መቀመጧን ትሬቨር ኖዋህም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ በሚገባ መስክረዋል።

በለሚ ታደሰ

#EBC #ebcdotstream #GERD #TrevorNoah #MiaMottley #Adwa #AfricaRising