Search

ለሀገራት ዕድገት መሠረት የሆነው አሰባሳቢ ትርክት

ሓሙስ ጥር 21, 2018 292

ኢትዮጵያውያን ከልዩነቶቻቸው ይልቅ አያሌ የጋራ ድሎች፣ ታሪኮችና እሴቶች ቢኖሯቸውም፤ አንድነታቸውን የሚያጠናክር የጋራ ብሔራዊ ትርክት ግን በሚገባው ልክ አልፈጠሩም።

ለሺህ ዓመታት የዘለቀ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት አለመፍጠራቸው፣ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የመገንባት ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድር ቆይቷል። 

የወል ትርክት ለአንድ ሀገር ሕዝብ የመዳረሻ አቅጣጫ መጠቆሚያ፣ የጋራ ማንነት መገለጫ እና ሀገራዊ መታወቂያ መሆኑን የሚናገሩት የማኅበረሰብ ልማት እና የተቋማት ሕክምና ልዩ ባለሙያው አቶ ዘላለም ይትባረክ፤ የህዝቦችን አብሮነት ለማጽናትም ትልቅ መሳሪያ ነው ይላሉ። 

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ከጋራ እሴቶች ይልቅ በልዩነቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱ ሀገሪቱን ለማይገባ የእርስ በርስ ግጭት እና አለመግባባት ዳርጓታል ያሉት አቶ ዘላለም፤ ይህን ክፍተት ለመሙላት አሰባሳቢ ትርክት ላይ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

ይህ ትርክት እንደ አዲስ የሚፈጠር ሳይሆን፤ ካለፈው በጎ ታሪካችን፣ ከእንግዳ ተቀባይነታችን እና ከድል አድራጊነት ታሪካችን ተወስዶ፣ ዛሬ ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተቀምሮ የሚሰናዳ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ያደጉ ሀገራት ሁሉ ወደ ዕድገታቸው የሄዱበት መንገድ የተቃኘው በገነቡት ትርክት ነው ያሉት ባለሙያው፤ ትርክት ለአንድ ሕዝብ በእርግጥም ለጋራ ግብ መግባቢያ፣ መተሳሰሪያ እና መወከያም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።

ትርክት በሕዝቦች መካከል ያለውን ልዩነት እንደ ውበት ተጠቅሞ የወደፊት የጋራ ራዕይን መፍጠር እንደሆነም ተናግረዋል።

ግለሰባዊ ዕድገት ለማኅበረሰብ ልማት መሠረት እንደሆነ ሁሉ፣ በትርክት የተቃኘ ጠንካራ ሕዝብ ደግሞ ለጠንካራ መንግሥት ግንባታ ዋስትና መሆኑን ገልጸዋል። 

ገዢ ሀገራዊ ትርክት መፍጠር መቻል በወደፊት የለውጥ ጉዟችን መንገራገጭ ሲያጋጥመን እርስ በርስ በመደጋገፍ፣ እንደ ሀገር ተሰናስለን አብረን መቆም የምንችልበትን አቅም ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አለውም ብለዋል።   

በአሁኑ ወቅት እየተደረጉ ያሉ የሀገራዊ ምክክር እና የጋራ ትርክት ግንባታ ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እያደረገው ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክርም አቶ ዘላለም ጠይቀዋል።

በላሉ ኢታላ 

#EBC #EBCDotstream #Ethiopia #Unity #ኅብረ_ብሔራዊት_ኢትዮጵያ