የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባለፉት ሰባት ዓመታት በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ያከናወናቸው የሪፎርም ትግበራ ሥራዎች ውጤታማ እንደነበሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ገለጹ።
የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሥር የሚገኘውን የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ያስገነባውን አዲስ ሕንጻ የጎበኙ ሲሆን፤ በአመራሮቹም ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ባካሄዳቸው ሥር ነቀልና ተከታታይ ተቋማዊ የሪፎርም ትግበራዎች በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል፣ አሠራርና አደረጃጀት አስደናቂ እመርታዎች የተመዘገቡ መሆናቸውን የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተናግረዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) የተለያዩ ሀገራት አቪዬሽን ደኅንነት የሥራ እንቅስቃሴዎችን የማየትና የመታዘብ እድል እንደገጠማቸው በመጠቆም፤ በኢትዮጵያ በዘርፉ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን ነው ብለዋል።
በአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ሥር የሚገኘው የአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፉ የታጠቃቸው ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎች ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተቀባይነትና ተወዳዳሪነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ መሃዲ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሀገሪቱ የአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር በማድረግ በኩል ከፍተኛ የአመራር ክትትል፣ ቁጥጥርና ቁርጠኝነት የተስተዋለ እንደነበርም መግለጻቸውን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለኢቢሲ በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡