Search

የ5ቱ ዓመታት ገፆች - ዘመኑን በዋጀ አገልግሎት የከተሜውን ህይወት ያቀለለው “መሶብ”ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ፣ በተለይም በዋና ከተማችን፣ እየታየ ያለው አስደማሚ የከተሜነት ትራንስፎርሜሽን እና ዘመናዊ የለውጥ ማዕበል የዘመናችን ትልቁ ማሳያ ሆኖ ብቅ ብሏል።

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 48

ሩቅ አስቦ እያደረ ያለው የኢትዮጵያ መደመር ትውልድ ሩቅ አዳሪ ህልሞችን ዕውን እያደረገ፣ ሩቅ እያደረ ይገኛል። ለነገው ትውልድ ነገን ምቹና ተወዳዳሪ እያደረገው ይገኛል።

ይህ የለውጥ ጉዞ ግዑዝ በሆኑ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ በማቅለል እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ ስር-ነቀል ለውጥ ማምጣትን ዋነኛ ግቡ አድርጎ እየተጋ ይገኛል።

የለውጡ መንግስት ትልቁ መገለጫ "ልማት ለሰዎች እንጂ ሰዎች ለልማት አይደሉም" የሚለውን ዕሳቤ መነሻ አድርጓል። ከዚህ ቀደም የነበረውን አድካሚ፣ ጊዜ አባካኝ፣ በቢሮክራሲ የተተበተበ እና ኋላቀር የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት ሙሉ በሙሉ ለማስተካከል፣ የለውጡ መንግስት ጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን በተግባር እያሳየ ነው።

የዚህ ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ ዋነኛ አንጓ የሆነው ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ዘመኑን የዋጀ አሰራር ለመዘርጋት እና ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተጀመረ የትውልድ ልቀት ፕሮጀክት ነው።

መንግስት የዜጎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ምህዳር ለማሸጋገር "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂን በጥልቀት በመንደፍ በትጋት እየሰራ ይገኛል።

ይህ ራዕይ ከተማዋ ዕለት በዕለት የምታስመዘግበውን ፈጣን ዕድገት እና «ስሉጥ ከተማ» (Smart-city) የመሆን ህልም በሚመጥን መልኩ፣ ቴክኖሎጂን ከነዋሪው የአኗኗር ዘይቤ ጋር እያዋሃደ ነው።

የዚህ ስትራቴጂክ አቅጣጫ እና የዘመን ዝላይ ትልቁ ማሳያ ደግሞ «መሶብ» የተሰኘው አዲሱ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ነው።

መሶብ፣ በኢትዮጵያውያን የባህል እሴት የጋራ ተጠቃሚነትን፣ አብሮነትን፣ እንግዳ ተቀባይነትን እና ማዕድን የሚያንፀባርቅ እጅግ ጥልቅ ትርጉም ያለው ቃል ነው።

ዛሬ ላይ ይህ ቃል አዲስ ትርጓሜ አግኝቶ የዘመናዊነት፣ የቅልጥፍና እና የስሉጥ አገልግሎት (Smart Service) ህያው ተምሳሌት ሆኗል።

የመንግስት አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል (E-government) መቀየር የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና ግልፅ ከማድረጉም በላይ፣ የሙስና እድሎችን በመቀነስ ረገድ አስደናቂ ውጤት እያመጣ ነው።

ኦንላይን የሚሰጡ የመንግስት አገልግሎቶች 737 መድረሳቸውና የዲጂታል ክፍያ ዝውውር ማደጉ ይህንኑ ያረጋግጣል።

ይህን የአዲስ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በማዕከል ደረጃ እና በዘጠኝ ክፍለ ከተሞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጁ ማዕከላት ተገንብተው ወደ ስራ ገብተዋል።

ከዚህም ባለፈ፣ ቋሚ ማዕከላት ድረስ መምጣት ለማይችሉ በተንቀሳቃሽ አውቶብስ (Mobile Bus) የተደራጀ፣ ፈጠራ የታከለበት አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።

ይህ የዘመን ዝላይ ያመጣው ስሉጥ አገልግሎት በህብረተሰቡ ዘንድ ያሳደረው ተፅዕኖ እጅግ አዎንታዊ እና የሚያኮራ ነው።

በዳሰሳ ጥናቶች እንደተረጋገጠው፣ የአገልግሎቱ ተገልጋይ ከ99 በመቶ በላይ እርካታ እንዳለው መመስከሩ የህብረተሰቡን ዳግም እምነት እና የትውልዱን የዲጂታል ልቀት የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው።

በማጠቃለል፣ የመሶብ ዲጂታል አገልግሎት የ«ስሉጥ ከተማ» ራዕይ መሬት ላይ የወረደበት ተግባራዊ ማሳያ ነው።

ትላንትናን በመሰልቸት ስናነሳው የነበረውን ስርዓት ወደ ላቀ የእርካታ ደረጃ ማሸጋገር መቻላችን፣ የ"5 ሚሊዮን ኮደሮች" ንቅናቄና በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ የታጀበው ሀገራዊ ጉዞ ትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኑን ያሳያል።

መሶብ ስሉጥ ከተማን በስሉጥ አገልግሎት እያጀበ፣ የትውልድ ልቀትን በተግባር የሚያረጋግጥ የዘመናችን ብሩህ ፋና ወጊ ብርሃን ነው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ