ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን የነባሩን ፖሊሲ መዋቅራዊ ክፍተቶች ለማረም፣ በከተሞች የታዩ አበረታች የሪፎርም ለውጦችን ለማጽናት እና የከተማ-ገጠር ትስስርን ለማጠናከር በአዲስ መልክ የተዘጋጀው አዲሱ የከተማ ልማት ፖሊሲ ከዛሬ ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁ ለኢትዮጵያ የከተማ አስተዳደር ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ኩነት ነው።
ይህ ፖሊሲ በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት በከተማ ልማት ዘርፍ የተመዘገቡትን ተጨባጭ የሪፎርም ስራዎች እና የመሬት ላይ ስኬቶች መሠረት አድርጎ የተቀረጸ የነገዋን ኢትዮጵያ ገጽታ የሚወስን ስትራቴጂካዊ ሰነድ ነው።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ከተሞችን የድህነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት እና የስራ አጥነት ማዕከል ከማድረግ ወጥቶ የብልጽግና ማሳያ የኢኮኖሚ ምንጭ እና የእድገት ሞተር ለማድረግ የተወሰዱት ቁርጠኛ እርምጃዎች ዛሬ ለፖሊሲው መጽደቅ ዋነኛ ስንቅ ሆነዋል።
ቀደም ሲል ከተሞች አምራች አይደሉም ጥገኞች ናቸው በሚል መገለጫቸው ግብርና ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጎ የከተማ ታሪክን የሚመጥን እድገት ሳይመዘገብ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ባለፉት አምስት ዓመታት ግን ከተሞች የፈጠራ፣ የፍጥነት እና የከፍተኛ ኢኮኖሚ ማዕከል ወደ መሆን ተሸጋግረዋል።
በዚህ የለውጥ ጉዞ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው እና በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ተጀምሮ ወደ 76 በሚጠጉ ከተሞች እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት፣ የከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ሰውን ማዕከል ያደረገ አዲስ የመኖሪያ ዘይቤ እና ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ የቻለ ትልቅ ስኬት ነው።
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ከተሞች 74 በመቶ የሚሆኑት ከደረጃ በታች እና መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው፣ 24 በመቶ ያህሉ ብቻ ከደረጃው ጋር እኩል የሚጓዙ የነበሩ ሲሆን ባለፉት ዓመታት የተሰሩት ስራዎች ግን ድሃውን ከከተማ ሳያፈናቅሉ፣ የፕላስቲክ ቤቶችና መታጠቢያ የሌላቸውን ሰፈሮች እዛው ባሉበት በማልማት የዜጋውን ክብር የመለሱ ሆነዋል።
የተሸከርካሪ ባለቤቶች ጥቂት በሆኑበት ሀገር ተሸከርካሪዎችን ብቻ ታሳቢ ያደርግ የነበረውን የድሮ አሰራር በመቀየር፣ ሰፊ የእግር ጉዞ መንገዶች (Walkways)፣ ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ አረንጓዴ ፓርኮችና የህፃናት መጫወቻዎችን በመገንባት ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ ተደርጓል።
በተጨማሪም የከተማ ነዋሪውን ዋነኛ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ በመንግስት አስተባባሪነት እንዲሁም የግል ሴክተሩን፣ ሪል እስቴትአልሚዎችንና የህብረት ስራ ማህበራትን በማሳተፍ መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸዉ አቅርቦትን ለማስፋት የተደረገው ጥረት የከተማ ልማት ዘርፉ ምን ያህል በተጠናከረ ፍጥነት ላይ እንደሚገኝ ያሳያል።
ዛሬ የጸደቀው አዲሱ የከተማ ልማት ፖሊሲ ወደፊት በሚኖረው አዎንታዊ ተፅዕኖ ሲመዘን በሀገራችን የረጅም ጊዜ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መዋቅር ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ነው።
በፖሊሲው ትግበራ የሚመጣው ትልቁ ለዉጥ ከተሞች በኢኮኖሚ ራሳቸውን የመቻል እና የገቢ ምንጫቸውን የማሳደግ አቅም ያገኛሉ፡፡ ከተሞች ከዚህ ቀደም የነበራቸውን የድህነት እና የሴፍቲኔት መገለጫ ሙሉ በሙሉ በመቀየር፣ ማዕከላዊ በሆነ መንገድ ራሳቸውንና የየአካባቢያቸውን የተፈጥሮ ጸጋ መነሻ አድርገው ኢኮኖሚ የሚያመነጩበትን ዕድል ይፈጥራል።
ይህ መዋቅራዊ ሽግግር ከተሞች የራሳቸውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማት ወጪዎች መሸፈን እንዲችሉ ከማድረጉም በላይ በመንግስትም ሆነ በዜጎች ደረጃ ተጨማሪ የገቢ አማራጮችን እና የስራ እድሎችን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።
በተጨማሪም የሀብት ክፍፍል ፍትሃዊነትን እና ማህበራዊ መረጋጋትን ማረጋገጥ መቻሉ ነው፤ የሚሰሩት ዘመናዊ መሰረተ ልማቶች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸዉን ፣ መካከለኛውን እና ሀብታሙን እኩል የሚያስተናግዱ በመሆናቸው ማህበራዊ መገለልን ያስቀራሉ።
ከሁሉም በላይ ግን ፖሊሲው አረንጓዴ መሰረተ ልማትን እና የማይበገሩ ከተሞችን መገንባትን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ አረንጓዴ ስራዎችን በመፍጠር ረገድ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው።
ይህ አዲስ ፖሊሲ ከአሁን በኋላ ዝቅተኛ መሰረተ ልማትን የማይቀበል እና የላቀ ስብዕና ያለው ትውልድ የመገንባት ትልቅ ታሪካዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጠቃሜታም አለው።
በበረከት ሽመልስ