Search

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስት የብድር ስምምነቶችን ጨምሮ አምስት ረቂቅ አዋጆችን አጸደቀ

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 78

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ ልዩ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በልዩ ስብሰባው ላይ በስፋት መክሮ ያጸደቃቸው ሦስቱ የብድር ስምምነቶች ለዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ የእድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈጸሚያ፣ ለሁለተኛው የማህበረሰብ ተኮር የመሬት አያያዝ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የመስኖ ልማት ለዘላቂ ምርታማነት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውሉ ናቸው።

ከተጠቀሱት የብድር ስምምነቶች በተጨማሪ ምክር ቤቱ የምግብ ሥርዓት እና ሥርዓተ ምግብ ረቂቅ አዋጅን እንዲሁም የግብርና ቢዝነስ ካምፓኒ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ በጥልቀት መርምሮ አዋጆቹን በሙሉ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ መርምሮ ካጸደቃቸው ሕጎች መካከል በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ የእድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የሚውለው የብድር ስምምነት አዋጅ አንዱ ነው።

ይህ ብድር መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች የጀመራቸውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች ለማበረታታትና ለመደገፍ እንዲቻል እገዛ የሚያደርግ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ መሰረት ኃይሌ ለመድረኩ አብራርተዋል።

ከተጠቀሰው ዓለም አቀፍ የልማት ማህበር የተገኘው ይህ ብድር፣ መንግሥት የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች በስኬት ለማስቀጠልና የፌዴራል መንግሥትን በጀት በቀጥታ ለመደገፍ የሚያግዝ ሲሆን፣ ከወለድ ነጻ ሆኖ በሰላሳ አንድ ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑን ወይዘሮ መሰረት ገልጸዋል።

ይህ የፋይናንስ ድጋፍ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብር ይበልጥ በማጠናከር፣ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ሥር ሰዶ የቆየውን መዋቅራዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት እና አስተማማኝ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ሚኒስትር ዴኤታዋ በዝርዝር አስገንዝበዋል።

የምክር ቤት አባላቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ለዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ የእድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የሚውለውን የብድር ስምምነት አዋጅ በሁለት ድምጸ-ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምፅ አጽድቀውታል።

በአባዲ ወይናይ