ጂንካ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶችን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የዩኒቨርስቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አገኘሁ ተሻገር በተገኙበት አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በዛሬው ዕለት ካስመረቃቸው ፕሮጀክቶች መካከል የመምህራን መኖሪያ ሕንጻ፣ የመመረቂያ/ስብሰባ አዳራሽ፣ የአስተዳደር ሕንፃ እና የተማሪዎች ካፌቴሪያ ይገኙበታል፡፡
የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶቹን መርቀው የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አገኘው ተሻገር፤ ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል ከነበሩበት የመማር ማስተማርና የመሠረተ-ልማት ችግሮች ወጥቶ ለዚህ ስኬት መብቃቱን አንስተዋል።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን የአካባቢውን ነዋሪዎች የሚጠቅሙ ሥራዎችን በመሥራት ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
ከግንባታ ባለፈ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ በ2030 በዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት ተወዳዳሪ የሚሆኑ ተማሪዎችን መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራና የራሱን ገቢ በማስገባት ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እንደሚተጋም አፈ-ጉባኤው ገልጸዋል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ ይትባረክ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በፕሮጀክቶቹ ግንባታ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ አካላትን ሁሉ አመስግነው፣ በቀጣይም በግቢው ውስጥ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት ካከናወነው የፕሮጀክቶች ምረቃ ማግስት፣ በነገው ዕለት የ6ኛ ዙር የተማሪዎች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት እንደሚያካሂድ ታውቋል።
በአያንቱ እምሩ