Search

በጋምቤላ ክልል ለአረንጓዴ አሻራ ዝግጅት ተደርጓል፦ የክልሉ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 54

በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ16 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድሪው ቱት አስታውቀዋል።

አቶ አንድሪው ቱት እንደገለጹት፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ቀጣይነት ባለው መልኩ ችግኞችን በመትከል በረሃማነትን ለመከላከል፣ ተስማሚ ሥነ-ምህዳር ለመፍጠር እና የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ የሚያግዙ ተግባራት ተከናውነዋል።

በክልሉ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያግዙ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችም በመርሃ ግብሩ ውስጥ በትኩረት መካተታቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም የተራቆቱ መሬቶች እንደገና እየተመለሱ በመሆናቸው የአፈር ለምነትን ለማሻሻል አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘንድሮው መርሃ ግብር የቀደሙትን ስኬቶች በማስፋት የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማጠናከር እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኙ የደንና የፍራፍሬ ችግኞችን በስፋት ለመትከል ዝግጅት መደረጉን አክለዋል።

በተጨማሪም በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የችግኝ መትከያ ቦታዎችን በመለየት የመትከያ ጉድጓዶችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዘንድሮ የሚተከሉት ችግኞች የምግብ ሉዓላዊነትን ለማጠናከር እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኙ የፍራፍሬ ችግኞች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚተገበር ተገልጿል።

በሚፍታህ አብዱልቃድር