ከሰኔ 23 እስከ ሐምሌ 16 ቀን በበይነ መረብና በወረቀት የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የፈተና ስርቆትን የሚጠየፍ ትውልድ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይም በፈተናው ሂደት ፈተና ለመስረቅም ይሁን ለማሰረቅ በሚሞክሩ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለፈተናው ስኬታማነት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው፣ የፈተናው አጠቃላይ ሂደት ደህንነቱ የተጠበቀ፣ በሰላምና በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካል በተባበረ እና በተቀናጀ ሁኔታ መስራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች መካከል በአብዛኛው በበይነ መረብ የሚሰጥ መሆኑና የፈተና ተቋማቱም በርከት ባለ ሁኔታ በክልል ደረጃ የተደራጁ መሆናቸው ፈተናውን ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የፈተናውን ደህንነት የማረጋገጥ ጉዳይ ከሌላው ጊዜ በተለየ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚያስፈልግ ሚኒስትር ዴኤታዋ አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ በበኩላቸው፣ የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና በጋራ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ዘርፉ ተገቢውን ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
ሀገር አቀፍ ፈተናው ውጤታማ እንዲሆንና በታሰበው አግባብ እንዲጠናቀቅ በታማኝነትና በትብብር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግም ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ አክለው ገልፀዋል፡፡
የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከሰኔ 23 እስከ ሐምሌ 16 በበይነ መረብና በወረቀት እንደሚሰጥ አስታውሰዋል።
ይህንኑ ፈተና ለመውሰድ 563,501 ተፈታኞች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ውስጥ 306,456ቱ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ 257,045ቱ ደግሞ የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡