Search

ዓለም ተቀይሯል፤ "ዐይናፋር" ዲፕሎማሲን የተሻገረው አዲሱ ምኅዳር

ዓርብ ጥር 22, 2018 84

ዓለም ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ሲመራበት የነበረው የሊበራል የዲፕሎማሲ ሥርዓት እየተናጋ፣ ሀገራት በሕግ ሳይሆን "በአቅም" እና "በጥቅም" ብቻ የሚደራደሩበት አዲስ ምዕራፍ ተጀምሯል።
በዚህ እጅግ ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች በሆነ የዓለም አሰላለፍ ውስጥ፣ ስትራቴጂካዊ ስፍራን መያዝና የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ መጠቀም የብሔራዊ ጥቅም ዋነኛ መገለጫዎች ሆነዋል።
ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት፣ በዚህ የጥቅም ፖለቲካ ውስጥ "ዐይናፋር" መሆን ቦታ የሚያሳጣ ከመሆኑም በላይ፣ ብሔራዊ ጥቅምን አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪው ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፣ የዓለም አቀፍ ዕርዳታና ድጋፎች በማንኛውም ጊዜ በለጋሾች ፍላጎት ሊቋረጡ እንደሚችሉ የታመነበት ጉዳይ ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ይህንን አስቀድማ በመገንዘብ፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የጀመረችው የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና በስንዴ ልማት ራስን ለመቻል የምታደርገው ጥረት አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ በሌሎች እጅ ላለመውደቅ የተደረገ ትልቅ ቅድመ-ዝግጅት ነው።
በውጭ ኃይሎች ላይ ጥገኛ የሆነን ኢኮኖሚ ወደ ራስ መተማመን የመቀየር ሂደት፣ ሀገራዊ ጥቅምን ከማስከበር ባሻገር በዲፕሎማሲው መድረክ ጎልቶ ለመውጣት የሚያስችል የጥንካሬ መሠረት ሆኖ ያገለግላል።
ዓለም ወደ ግላዊ ጥቅም በምታዘነብልበት በዚህ ዘመን፣ ኢትዮጵያ በግብርና፣ በኢኮኖሚና በንቁ ዲፕሎማሲ የጀመረቻቸው ስትራቴጂካዊ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው የህልውና ጉዳይ ነው።
 
በአዝመራው ሞሴ