በኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ በክብር እንግድነት የታደሙት የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ (ዩኤስ-አፍሪኮም) አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አንደርሰን፥ አሜሪካ እና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ የሽብር ስጋቶችን ለመከላከል በጋራ የመሥራት ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ።
የዩኤስ-አፍሪኮም አዛዡ ከአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ላንዶው ጋር በመሆን በቢሾፍቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና መስሪያ ቤትን እና የጥቁር አንበሳ ኤክስፖን ጎብኝተዋል።

ጄኔራል ዳግቪን አንደርሰን፥ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና እንደ አል-ሸባብ እና አይሲስ ያሉ የጋራ የሽብር ስጋቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በተለይ በቀይ ባሕር አካባቢ ቀጣናውን ለማናጋት የሚደረገው የሁቲዎች እንቅስቃሴም አሳሳቢ መሆኑን አንስተዋል።
እነዚህን የደኅንነት ስጋቶች በአስተማማኝ ሁኔታ ለመመከት የሁለቱ ሀገራት ቅንጅት እና ወታደራዊ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ባደነቁበት አስተያየታቸውም፣ ተቋሙ ከአሜሪካ አየር ኃይል ቀድሞ መመሥረቱን ጠቅሰዋል። “የእኔ ሀገር አየር ኃይል የተመሰረተው በ1947 ሲሆን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ግን በ1935 ተቋቁሟል” በማለት ለአንጋፋው ተቋም ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል።

አሜሪካዊው አብራሪ ኮሎኔል ጆን ሮቢንሰን በፋሺስት ወረራ ወቅት ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጥሪ ምላሽ በመስጠት የኢትዮጵያ አየር ኃይል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን በማቋቋም ያደረገው አስተዋጽኦ ለዛሬው የሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ወዳጅነት መሠረት መሆኑን አውስተዋል።
አቪዬሽን ድንበር እና ባህል የማይገድበው የጋራ ቋንቋ መሆኑን የተናገሩት የዩኤስ-አፍሪኮም አዛዡ፣ በኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ከዩኤስ ባህር ኃይል (ማሪን ኮር) የመጡ ቪ-22 (V-22) አውሮፕላኖች በመሳተፋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ በተለይ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ልማት ላይ እያደረገችው ያለው ኢንቨስትመንት ለቀጣዩ ትውልድ ተስፋ የሚሰጥና ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ዕድሎችን የሚፈጥር መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
በላሉ ኢታላ
#EBCDotstream #Ethiopia #USA #militarycooperation #EthiopianAirForce #usmarinecorps