ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ያላት ሚና ከመልክዓ ምድር አቀማመጥ የላቀ ነው። የቀጣናው አስተሳሳሪ ኃይል በመሆኗ የዓለም አቀፍ ኃይሎች እና ለጎረቤት ሀገራት ዋነኛ የትኩረት ማዕከል ነች።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ፤ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ አውሮፓ፣ ከእስያ እስከ ምሥራቅ አውሮፓ ያሉ ሀገራት የኢትዮጵያን የስበት ማዕከልነት በመገንዘብ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በልዩ ትኩረት እየተከታተሏት ይገኛሉ።
ለመሆኑ ኢትዮጵያን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የስበት ማዕከል ያደረጓት ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
1. የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ
አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት (AU) እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) መቀመጫ ናት። ይህ ደግሞ ከተማዋን ከኒው ዮርክ እና ብራስልስ ቀጥሎ የዓለማችን ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል ያደርጋታል።
ማንኛውም አህጉራዊ አጀንዳ ያለ ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ ፍፁም ሊሆን እንደማይችል በተግባር እያሳየች ትገኛለች። በተለይም በቅርብ ዓመታት የተከናወኑት የአዲስ አበባ የመዘመንና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ያላትን ተመራጭነት ይበልጥ አሳድጎታል።
2. የሰላም እና የጸጥታ ምሰሶነቷ
ኢትዮጵያ በቀጣናው ካሉት ሀገራት ግዙፍ እና ጠንካራ የመከላለያ ሠራዊት በመገንባት ቀዳሚዋ ነች። በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳንና በአቢዬ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የተጫወተችው ሚና ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ ሆኖ ተገኝቷል። በተመድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥም ቋሚ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ኢትዮጵያ ተመራጭ ነች።
በተለይም ሽብርተኝነትን በመመከት ረገድ ያላት ልምድ ለምሥራቁም ሆነ ለምዕራቡ ዓለም ታማኝ የጸጥታ አጋር አድርጓታል። ኢትዮጵያ የሕንድ ውቅያኖስም ሆነ የቀይ ባሕር የክብር ዘብ ናት።
3. የኢኮኖሚ እና የገበያ አቅሟ
ከ120 ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ሁለተኛዋ ባለ ብዙ ሕዝብ ሀገር ናት። ይህ ቁጥር ብቻ ሳይሆን የፈጠራ አቅም ያለው ወጣት የሚበዛበት በመሆኑ፣ ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ግዙፍ የገበያ መዳረሻነት ተመራጭ ያደርጋታል።
4. የኃይል እና የመሠረተ ልማት ትስስር
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቀጣናውን ሀገራት በኤሌክትሪክ እያስተሳሰረ ይገኛል። ኢትዮጵያ ለሱዳን፣ ለጅቡቲ እና ለኬንያ ኃይል ማቅረብ መጀመሯ የቀጣናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠናክረዋል። በሌላ በኩል፣ የፓን አፍሪካኒዝም ምልክት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከዓለም ጋር በማገናኘት ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
5. ስትራቴጂካዊ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ
ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕርና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ካለው የዓለም አቀፍ የንግድ መስመር (Bab-el-Mandeb) ጋር ያላት ቅርበት፣ በቀጣናው ጂኦ-ፖለቲካዊ ሽኩቻዎች ውስጥ የማይታለፍና ተፈላጊ እንድትሆን ያደርጋታል።
ኢትዮጵያ የራቀችበት የቀይ ባሕር ቀጣና ምን ያህል ቀውስ ውስጥ እንደሚገባ ባለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት የታየ እውነታ ነው። ለዚህም ነው በቀይ ባሕር ላይ ትኩረት ያደረጉ ኃያላን ኢትዮጵያን መግፋት የማይችሉት።
በአጠቃላይ፣ ተፈጥሮአዊ አቀማመጧ እና በንቁ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚመራው ዲፕሎማሲዋ ኢትዮጵያን የዓለም ዓይን ማረፊያ አድርጓታል።
በለሚ ታደሰ