የክረምት ወቅት ይዟቸው የሚመጣ ጥቅሞች እንዳሉ ሁሉ ጉዳቶችም ስመኖራቸው ይነገራል።
ከጉዳቶቹ አንደኛው የጎርፍ አደጋ እንደሆነ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የመረጃ ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ፍራኦል በቀለ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።
በተጨማሪም መሬቱ ውሃ በሚጠግብበት ጊዜ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል ነው ዶ/ር ፍራኦል የተናገሩት።
የኢትዮጵያ መልክዓምድር የተለያየ እንደመሆኑ በክረምት ወቅት ለተለያዩ አደጋዎች ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ አንዳንድ ቦታዎች መኖራቸውን ነው የገለፁት።
በእርሳቸው የሚመራው ተቋም በዚህ ላይ እንደሚሠራ እና በሀገሪቱ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ክልሎች፣ ዞኖች እና ወረዳዎችን መለየቱንም ነው የተናገሩት።
ተቋሙ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መሰል አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት የመከላከል፤ ከተከሰቱም በኋላ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች እንደሚሠራ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ በርካታ ተፋሰሶች መኖራቸውን ጠቅሰው በተለይ በአዋሽ ተፋሰስ ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል እና አደጋው ከደረሰ በኋላም ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ስለሚከናወኑ ሥራዎች አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮማንደር አህመድ መሀመድ በበኩላቸው፥ መዲናዋ የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱባት እንደሆነች አንስተው ለአደጋ ተጋላጭ ስለመሆኗም አክለዋል።
በከተማዋ የሚያጋጥሙ 10 የተለያዩ አደጋዎች ስለመኖራቸው የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ ከእነዚህ ውስጥ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት፣ እሳት እና የትራፊክ አደጋ በተለይ በክረምት ወቅት አሳሳቢ ስለመሆናቸው አንስተዋል።
በመዲናዋ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች በጥናት ተለይተው የማቅለያ ሥራዎች ስለመከናወናቸውም ነው የገለፁት።
በሜሮን ንብረት
#ኢቢሲ #ኢቢሲዶትስትሪም #ክረምት #የአደጋስጋት #ቅድመመከላከል