ውብዓለም አሥራት ትባላለች፤ የምትኖረው ሐዋሳ ከተማ ነው።
እናቷን ገና የሁለት ዓመት ሕፃን እያለች ያጣችው ይህቺ ወጣት፣ “በሕይወቴ ብዙ ፈተናዎችን አልፌያለሁ፤ የእኔ ሕይወት ፈተና የጀመረው ከሕፃንነቴ ነው፤ ምክንያቱም የእናት ፍቅር አላውቅም” ትላለች።
በአባቷ እና በእንጀራ እናቷ እጅ ያደገችው ውብዓለም፣ ቤት ውስጥ ብዙ መከራዎችን እያለፈች ጠንክራ ትምህርቷን ቀጠለች።
በመሐል አባቷ ከሐዋሳ ወደ ሌላ ከተማ ሲሄድ ሕይወትን ለብቻዋ ለመጋፈጥ እንደወሰነችም ለኢቢሲ ዶትስትሪም ትናገራለች።
ሰው ቤት ተጠግታ ትምህርቷን እየተማረች የነበረ ቢሆንም በመሐል ኑሮው ሲከብዳት ትምህርቷን ለማቋረጥ ወሰነች፤ ነገር ግን ትምህርት ቤቷ ባደረገላት ድጋፍ ትምህርቷን ሳታቋርጥ መማሯን ትናገራለች።
ውብዓለም ከሰው ቤት ወጥታ ሕይወት እየከበዳትም ቢሆን የኮሌጅ ትምህርቷን ቀጠለች። የኮሌጅ ሕይወት የበለጠ ሲከብዳት ደግሞ ትምህርቷን ሙሉ ለሙሉ ልታቋርጥ ወሰነች።
በዚህ መሐል ታዲያ ጄሪ ሞላ የተባለች እንስት በአንድ ካፌ ውስጥ ተቀጥራ እየሠራች ትምህርቷን እንድትቀጥል ዕድሉን አመቻቸችላት።
ውብዓለም ትምህርቷን በማታ እየተማረች ለመሥራት ብትወስንም የሥራ ዕድሉን የሰጠቻት የማኪታ ካፌ ባለቤት ወ/ሮ ፅዮን ሞላ ትምህርቷን በመደበኛነት እንድትማር ከኮሌጁ ጋር በመነጋገር አመቻቸችላት።
ውብዓለምም በሥራዋም፣ በትምህርቷም ተግታ ውጤታማ ሰው ለመሆን በቃች።
በሥራ ሥነ-ምግባሯ በአለቆቿ የምትመሰገነው ወጣቷ፣ የሕይወት ውጣ ውረዶችን አልፋ ከአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በቢዝነስ ማኔጅመንት 3.83 በማምጣት በማዕረግ ተመርቃለች።
በኮሌጁ ባስመዘገበችው ከፍተኛ ነጥብም የወርቅ ማዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች።
“የማኪታ ካፌ ባለቤት ወ/ሮ ፅዮን ሞላ እና የማኔጅመንት አለቆቿ እንደ አሠሪ እና ሠራተኛ ሳይሆን እንደቤተሰብ ሲደግፉኝ ነበር” ስትል ውብዓለም ምስጋናዋን አቅርባለች።
በሔለን ተስፋዬ
#EBC #ebcdotstream #hardwork #education #endurance