Search

በኢትዮጵያ ያለውን ሰላም በማጠናከር ለማፅናት የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡- የሰላም ሚኒስቴር

በኢትዮጵያ ያለውን ሰላም በማጠናከር ለማፅናት መላው ህብረተሰብ እያደረገው ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ እድሪስ ጥሪ አቅርበዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ከፌደራል እንዲሁም ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የጸጥታ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮችን "ሰላምን ማፅናት፣ ለሀገራዊ ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዳማ እያወያየ ነው። 

ተሳታፊዎቹ አሁን በሀገሪቱ ያለውን ሰላም በማጠናከር ማፅናት በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ እየተወያዩ ነው።

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ እድሪስ መድረኩን ሲከፍቱ፥ "አሁን በሀገሪቱ ያለው ሰላም የፀጥታ ተቋማት ከመላው ህብረተሰብ ጋር በቅንጅት በመሥራታቸው የተገኘ ነው፤ በቀጣይም ይህን ሰላም በማጠናከር ለማፅናትም ህብረተሰቡን ማሳተፍ ይገባል" ብለዋል።

በሀገሪቱ የፀጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎችም ከህዝቡ ጋር በቅንጅት በተከናወነ ሥራ አንፃራዊ ሰላም በመገኘቱ ህብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ የዕለት ተለት ሥራውን ማከናወን ችሏል፤ በዚህም በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፎች ለውጥ እየታየ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ህብረተሰቡን የሚያማርሩ ጉዳዮችን ፈጥኖ በመረዳት ግጭቶች እንዳይፈጠሩ፤ ከተፈጠሩ ደግሞ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን በመጠቀም እንዳይባባሱ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። 

በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች መፍትሄ ለመፈለግ በአዳማ እየተካሄደ ያለው ውይይት ነገም የሚቀጥል ሲሆን፤ በመድረኩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ አስዳደደር የፀጥታ መዋቅር ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በተስፋዬ ለሜሳ

#ኢቢሲ #ኢቢሲዶትስትሪም #የሰላምሚኒስቴር #ሰላምንማፅናት #ሀገራዊማንሰራራት