Search

4.9 ሚሊየን ቱሪስቶች መዲናችንን ጎብኝተዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ዓርብ ጥር 29, 2018 77

በአዲስ አበባ በቱሪዝም ልማት ፣ በተማሪዎች ምገባ፣ በትራንስፖርት እና በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
ከንቲባ አዳነች ለከተማው ምክር ቤት ባቀረቡት የአፈፃፀም ሪፖርት፤ ባለፉት ስድስት ወራት ከተማችንን ይጎበኛሉ ተብሎ ከታቀዱ 4.7 ሚሊየን የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች 4.9 ሚሊየን ቱሪስቶች መዲናችንን ጎብኝተዋል ብለዋል፡፡
በከተማዋ ሲከበሩ የነበሩ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ ባሕላዊ የአደባባይ በዓላት፤ እንዲሁም የስፖርትና የጤና ቱሪዝም መስፋፋት ከፍተኛ አበርክቶ የነበራቸው ሁነቶች መጎብኘታቸውንም ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት 150 የሚሆኑ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ኩነቶች አዲስ አበባ ላይ መካሄዳቸውን አመላክተው፤ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጻር የ50 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አመላክተዋል።
በአጠቃላይ ከሀገር ውስጥ እንዲሁም በተመሳሳይ 699 ሺህ 761 የውጭ ቱሪስቶች መጎብኘታቸው ጠቁመው፤ ከቱሪዝሙ ባለፉት ስድስት ወራት 155 ቢሊየን ብር ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
የተማሪዎች ምገባን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ ከ 940 ሺህ 329 በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ጥራቱን የተጠበቀ እና ጤናማነቱ የተረጋገጠ ምግብ እንዲመገቡ መደረጉን አስታውቀዋል።
ባለፉት 6 ወራት 14 ሺህ 133 ተሸከርካሪዎችን በማሰማራት በቀን በአማካይ 3.98 ሚሊየን ህዝብ በማጓጓዝ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ማሳለጥ እንደተቻለ አንስተዋል።
የብዙኃን ትራንስፖርት ድርሻ ከነበረበት 36 በመቶ ወደ 42 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
የትራንስፖርት መሰረተ ልማትን ከማስፋፋት አኳያ የከተማውን የትራንስፖርት ችግር በወሳኝነት ሊቀርፍ የሚችል የፈጣን አውቶብስ ትራንዚት የ’BRT B2’ ፕሮጀክት የ15.6 ኪ.ሜ የመንገድና የዴፖ ግንባታ ሥራም መጀመሩንም ገልጸዋል።
የትራፊክ ቁጥጥር እና የፓርኪንግ አስተዳደር ክፍያ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ አገልግሎቱን ማዘመንና ማሻሻል ተችሏል፡፡
የሞተር አልባ ትራንስፖርትን ከማስፋፋት አኳያ ሰፊ ፕሮጀክት እየተተገበረ መሆኑንም ከንቲባ አዳነች አስታውቀዋል።