ሰላም የብሔራዊ ጥቅም ማስከበሪያ ጋሻ፣ ጠንካራ የውስጥ አንድነት ደግሞ የማይበገር የሉዓላዊነት ምሶሶ ነው።
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር ውስጣዊ ሰላምን ማጽናት እና ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ቀዳሚና ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል።
ልዩነቶች እና የፖለቲካ ጥያቄዎች ቢኖሩም እንኳ፣ ከውይይት ይልቅ ጠመንጃን መምረጥ ሀገራችንን ከፍተኛ ዋጋ ከማስከፈሉም በላይ ለዕድገቷ ትልቅ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል።
በዚህ ረገድ መንግሥት ለሰላም በሩን ክፍት በማድረግ እና ተነሳሽነቱን በመውሰድ ረጅም ርቀት መጓዙን፣ ይህም ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
እስከአሁን ጽንፍ ይዘው የቆሙ አካላትም በተመሳሳይ ልዩነቶችን ከሀገር በታች በማድረግ እና በሀሳብ የበላይነት በመሞገት ለውስጣዊ ሰላም መጽናት የዜግነት ድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ይገልጻሉ።
ፍትሐዊ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥም ሰላምን በማጽናት ሂደት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ፤ በዚህ በኩልም መንግሥት በሙሉ አቅሙ እየሠራ እንደሚገኝ ያነሳሉ።
በጥቅሉ የኢትዮጵያውያን ውስጣዊ አንድነት መጠናከር እንደ ሀገር የመደራደር አቅማችንን ከፍ በማድረግ ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር እንደ ብርቱ ክንድ ሆኖ እንደሚያገለግል ይታመናል።
በእርግጥም ሀገራችን አሁን ላይ እየተከተለችው ያለው ገቢር ነበብ (Pragmatic) ዲፕሎማሲ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን፣ ውስጣዊ ሰላምን ማጽናት ወቅቱ የሚጠይቀው እውነተኛ አርበኝነት ነው።
ሁላችንም ለሀገራችን ሰላም እና ለጋራ ብልጽግናችን በቁርጠኝነት እንነሳ።
በዘሃራ መሐመድ
#Ethiopia #peacebuilding #unity #nationalinterest #EthiopianBroadcastingCorporation #EBC