Search

በ54 የመኝታ ክፍሎቹ 54 የአፍሪካ ሀገራትን የሚያስጎበኘው የኩሪፍቱ የአፍሪካ መንደር

የአፍሪካውያንን ባህል እንዲሁም ታሪክ ማወቅ ለሚፈልግ ከሀገራችን ሳንወጣ ከአዲስ አበባም ብዙ ሳንርቅ አሸዋ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተንጣለለ ኮረብታማ ስፍራ የሚገኘው የኩሪፍቱ ሪዞርት እና ስፓ የአፍሪካ መንደር ተመራጭ መዳረሻ ነው።

የቅዳሜ መልክ የመዳረሻ ፕሮግራም የኩሪፍቱ የአፍሪካ መንደር ምን ይመስላል? በውስጡስ ምን ይዟል? የሚለውን ዳስሷል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ የአፍሪካን እሴት የሚያንፀባርቅ ስፍራ የሚያስፈልግ መሆኑን በማሰብ የተገነባ መንደር መሆኑን የኩሪፍቱ ሪዞርቶች ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮስ ጌታቸው ለኢቲቪ ተናግረዋል።

የአፍሪካውያንን ታሪክ፣ ባህሎች እና እሴቶች እንዲያጎላ ተደርጎ በተገነባው የኩሪፍቱ የአፍሪካ መንደር፤ በ54 የአፍሪካ ሀገራት የተሰየሙ 54 የመኝታ ክፍሎች ይገኛሉ።

በእያንዳንዱ ክፍል በር ላይ በሀገሩ የካርታ ቅርፅ ላይ ያረፈ ስያሜ ተሰቅሎ የሚታይ ሲሆን፤ ወደ ውስጥ ሲገባም የዚያን ሀገር ባህላዊ አልባሳትና መሳሪያዎች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ ታሪካዊ መፃሕፍት እና ጉልህ ክስተቶችን የሚያሳዩ ፎቶዎች ዙሪያውን ይገኛሉ።

በኩሪፍቱ የአፍሪካ መንደር የሚገኙ የመሰብሰቢያ አዳራሾችም የአፍሪካ ሕብረት እንዲመሰረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባበረከቱ መሪዎች የተሰየሙ ናቸው።

የአፍሪካውያንን ባሕሎች እና እሴቶች በማስተዋወቅ እንዲሁም እርስ በርስ በመጋራት የአህጉሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ ያሉ የተለያዩ ተግባራት በመንደሩ እንደሚከናወኑ አቶ ታዲዮስ ገልፀዋል።

ለአብነትም፥ በየጊዜው ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሼፎችን በማምጣት የሀገራቸውን ምግብ እንዲያበስሉ፤ የፋሺን ዲዛይነሮችን በመጋበዝ የፋሺን ሾው እንዲያሳዩ እንደሚደረግ የኩሪፍቱ ሪዞርቶች ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮስ ጌታቸው ጠቅሰዋል።   

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

#EBC #EBCdotstream #KuriftuResort #AfricanVillage