Search

ሕዝቦች የነፃነት ፋና፣ ዛሬ ደግሞ የማይቻለውን የመቻል አዲስ ተምሳሌት፦ ኢትዮጵያ

ሓሙስ የካቲት 05, 2018 31

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የታሪክ አድማስ ላይ ያላት ስፍራ በሁለት ጽኑ ዓምዶች ላይ የተገነባ ነው። ትላንት በቅኝ ግዛት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ለነበሩ ሕዝቦች ሁሉ ተስፋን የፈነጠቀች፣ የአህጉሪቱ የነፃነት ጮራና የጥቁር ሕዝቦች የኩራት ማማ ነበረች። ዛሬ ደግሞ ያንን ታሪካዊ የጀግንነት መንፈስ ወደ ልማት ድል በመቀየር፣ ተግዳሮቶችን በጽናት አልፋ የታላላቅ ስኬቶች መገኛና የአፍሪካ የ"መቻል ትዕምርት" ሆና በክብር ብቅ ብላለች።

ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ለነበሩ ሕዝቦች ሁሉ ተስፋን የፈነጠቀች፣ የማይጠፋ የነፃነት ፋና ናት። የታሪካዊው የዓድዋ ድል የነፃነት ማብሰሪያ ብቻ ሳይሆን፣ "ጥቁር ሕዝብ ማንኛውንም ግዙፍ ኃይል ማሸነፍ ይችላል" የሚል ታላቅ ሥነ-ልቦናዊ ድል የታወጀበትና የማይደመሰስ የታሪክ አሻራ ያረፈበት ነው። ትላንት በጦር ሜዳ የተመዘገበው ያ የጀግንነት ታሪክ፣ ዛሬ በልማትና በብልጽግና መስክ ለሚታዩ ስኬቶቻችን ሁሉ የማይነጥፍ የ"መቻል" ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ትላንት በጦር ሜዳ የታየው ጀግንነት ዛሬ መልኩን ቀይሮ በግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ በድምቀት እየተደገመ ይገኛል። ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ሥራዎች "የማይቻል የለም" የሚለውን የፅናት መንፈስ ለዓለም በተግባር ያሳዩባቸው ናቸው።

በተለይም ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የታታሪነት እና የብልሃት ትልቅ ማሳያም ነው። ከገንዘብ ማሰባሰብ እስከ ግንባታ ማጠናቀቂያ ድረስ የነበሩትን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች በጽናት በማለፍ፣ ኢትዮጵያ በገዛ አቅሟ ታላቅ ተዓምር መሥራት እንደምትችል አረጋግጣለች። ግድቡ የኃይል ምንጭ ብቻ ሳይሆን፣ ለአፍሪካውያን ሁሉ "እኛም እንችላለን" የሚል የዘመኑ የድል አርማ ነው።

የከተማ ውበትና የኮሪደር ልማት ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የአዲስ አበባንና የሌሎች ከተሞችን ገጽታ በመቀየር፣ የአፍሪካ ከተሞችን የተሳሳተ አመለካከት ቀይረዋል። ይህ ልማት የኢትዮጵያን ከፍተኛ የመፈጸም አቅም በተግባር ያሳየና ከተሞችን ለኑሮም ሆነ ለቱሪዝም ምቹ ያደረገ ድንቅ ስኬት ነው።

ለዓመታት በስንዴ እርዳታ ትታወቅ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ ራሷን ችላ ምርቷን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሯ ትልቅ የ"መቻል" ማረጋገጫ ነው። ይህ ስኬት የተፈጥሮ ሀብትን በብቃት በመጠቀም ረገድ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ድንቅ ተሞክሮ ሆኗል።

ኢትዮጵያ ትላንት ለአፍሪካ ፖለቲካዊ ነፃነት ፋና ወጊ እንደነበረች ሁሉ፣ ዛሬም ለኢኮኖሚ ነፃነትና ለብልፅግና የ"መቻል ትዕምርት" ሆና ቀጥላለች። ካለፈው የታሪክ ድል የወረሰችውን ጀግንነት በአሁኑ የልማት ግስጋሴ በማሳጀብ፣ ለአዲሲቱ አፍሪካ ሁለንተናዊ ብርሃን እየሆነች ትገኛለች።

በሰለሞን ከበደ

#EthiopianBroadcastingCorporation #Ethiopia #Africa #TheAfricaWeWant #Agenda2063