Search

"ውኃ አህጉራዊ ሀብታችን ነው፤ ለሰላምና ለልማት ሊውል ይገባል" - ማህሙድ አሊ ዩሱፍ

ቅዳሜ የካቲት 07, 2018 74

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በ39ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የአህጉሪቱን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ለውጥ ለማፋጠን የመሰረተ ልማት ትስስር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የዘንድሮው ጉባኤ መሪ ቃል በሆነው “ውሃ እና ንጽህና አጠባበቅ” ዙሪያ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ውኃ የአየር ንብረት ለውጥን ተቋቁሞ ለሰላምና ለልማት የሚውል የጋራ አህጉራዊ ሀብት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሊቀመንበሩ በአህጉሪቱ እየታየ ስላለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ስጋታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በተለይም በሱዳን እየተካሄደ ያለው ግጭት በአስቸኳይ ቆሞ ተጨባጭ የሰላም ስምምነት እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በሶማሊያ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተም የኅብረቱ የድጋፍና የማረጋጋት ተልዕኮ (AUSSOM) ዘላቂ ፋይናንስ በማግኘት የተመዘገቡ ስኬቶችን ማስቀጠል እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።
የወደፊት የአፍሪካን ጉዞ አስመልክተውም፣ የትምህርት ስርዓቱ በቴክኒክና ሙያ ክህሎት ላይ በማተኮር ወጣቶች በፈጠራ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የአህጉሪቱን ልማት ለማፋጠን የአፍሪካውያን ዲያስፖራዎችን በካፒታልና በዕውቀት ማስተሳሰር እንደሚገባ የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ለኢንዱስትሪ ልማት መሰረት መሆኑን አብራርተዋል።
አፍሪካ ጥሬ እቃዎችን ብቻ የመላክ ባህሏን አቁማ ምርቶቿን እሴት ጨምራ ለገበያ ማቅረብ እንዳለባት አሳስበው፣ ለዚህም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎና ዘላቂ የልማት ፋይናንስ መረጋገጥ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ