አፍሪካ የዓለም የታሪክ መድረክ ዋና ተዋናይ እየሆነች መምጣቷን የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ገልጸዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ገለጻ፣ ጣሊያንም ሆነች አውሮፓ ያለ አፍሪካ ንቁ ተሳትፎ የወደፊት ብሩህ ተስፋ ሊኖራቸው አይችልም።
አህጉሪቱ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት እና የእርሻ መሬት ብቻ ሳይሆን፣ ወሳኙን የሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ አሳስበዋል።
ጣሊያን በአውሮፓ እና በአፍሪካ መካከል እንደ ድልድይ ሆና ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፤ በተለይም ወጣቶች በቴክኖሎጂና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እንዲሰለጥኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው የመኖር እና የመሥራት ነፃነት ሊኖራቸው እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ወጣቶች በስደት ምክንያት ሀገራቸውን ሲለቁ የታሪክ እና የባህል ክፍተት እንደሚፈጠር በማስረዳት፣ ስደትን እንደ ብቸኛ አማራጭ ማየት "ራስ ወዳድነት" መሆኑን የካርዲናል ሮበርት ሳራህን ንግግር በመጥቀስ አስገንዝበዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ጥራት ያለው ትምህርት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ጠንካራ የኢንዱስትሪ ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የአፍሪካን ተሰጥኦ ወደ ውጭ ከመውሰድ ይልቅ በአህጉሪቱ ውስጥ እንዲያድግ የሚያደርግ አዲስ የልማት ሞዴል እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል።
"ሁልጊዜም ከአፍሪካ አዲስ ነገር ይገኛል" የሚለውን የጣሊያናውያንን አባባል በመጥቀስ፣ የማይቻለውን ነገር በትብብር ወደ እውነት ለመለወጥ እና ዓለምን ለማስደመም ቃል ገብተዋል።
በለሚ ታደሰ