Search

የአረንጓዴ አሻራ ዕድል የከፈተለት ወጣት

ወጣት አሸናፊ አራጌ ይባላል። የሕዳሴው ግድብ መገኛ በሆነው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነዋሪ ነው።
 
ወጣቱ ለችግኝ እንክብካቤ ሥራ ልዩ ፍቅር እንዳለው ይናገራል።
 
ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የአረንጓዴ አሻራ ዝግጅት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የበኩሉን ሲወጣ ቆይቷል።
 
በክልሉ አሶሳ ዞን አቡራሞ ወረዳ የአምባ 14 ቀበሌ ኗሪ የሆነው ወጣት አሸናፊ ከጓደኞቹ ጋር በመደራጀት ከአምስት ዓመታት በፊት ነበር ችግኝ የማፍላት እና የማቅረብ ሥራ የጀመረው።
 
በክልሉ የሚታወቁትን እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ የሆኑ ችግኞች ለግለሰቦች እና ለተለያዩ ተቋምት በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ችሏል።
 
 
 
 
የቀርቀከሃ፣ የማንጎ ፣ የአቮካዶ ፣ የብርቱካን እና የፓፓያ ችግኞች ወጣቱ ትኩረት ካደረገባቸው የችግኝ አይነቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
 
ወጣቱ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ያቀረባቸው ችግኞች በአሶሳ ከተማ እና አቅራቢያው በሚገኙ ቦታዎች ላይ በተለያዩ ጊዜያት በተከናወኑት የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሮች ላይ በስፋት ተተክለዋል።
 
ችግኞች በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን የቻለው ወጣቱ አሁን ኢኮኖሚያዊ አቅሙን በማሻሻል ኑሮውን በጥሩ ሁኔታ እየመራ ይገኛል።
 
ከዚሁ ከችግኝ ሽያጭ በሚያገኘው ገቢ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) በመግዛት ተጨማሪ የሥራ ዕድልን ፈጥሯል።
 
“ባጃጇ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ያበረከተልኝ ስጦታ ነች” ይላል አሸናፊ።
 
ከዚህም ባለፈ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራትም በዝግጅት ላይ መሆኑን ይናገራል። ለዚህ የሚረዳውን የከተማ መሬት መግዛቱንም ያስረዳል።
 
ከችግኞች ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ ከምንም በላይ የአዕምሮ እርካታን እንደሚፈጥርለት ነው የተናገረው።
 
ለየአካባቢው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የሚውሉ ብሎም የሕዳሴውን ግድብ ከደለል ለመጠበቅ የሚረዱ የልማት ሥራዎችን ማከናወን የእለት ተዕለት ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ያስረዳል።
 
ልክ እንደእርስ ሁሉ ሌሎች ወጣቶችም በችግኝ ዝግጅት ሥራ በመሳተፍ በአንድ በኩል ሀገራዊውን የአረንጓዴ ልማት እያገዙ በሌላ በኩል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ ወጣት አሸናፊ ጥሪውን አቅርቧል።
 
 
በጀማል አህመድ