በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ልዑክ በሀገሪቱ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ውይይት አካሂዷል።
ከተለያዩ አካላት ጋር ገንቢ ውይይት ሲካሄድ መቆየቱ ተገልጿል።
ከውይይቱ በኋላ አምስት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የምክክሩን አጀንዳ ተረክበዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፤ በሒደቱ ዳያስፖራው ማኀበረሰብን ማሳተፉ አካታች የሀገራዊ ምክክርን ለማካሄድ ያግዛል ሲሉ ለኢቢሲ ተናግረዋል።
በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ከ300 በላይ ሰዎች መሳተፋቸውንም ገልጸዋል።
በሂደት በሀገራዊ ምክክር የሚሳተፉ ተወካዮች እንደሚኖሩም ታውቋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በፌዴራል ደረጃ የሚካሄደው የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ዴሞክራሲያዊ ውይይትን ባህል ለማድረግ እና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ልማድን ለማዳበር እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በደቡብ አፍሪካው ውይይት በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የሀሳብ፣ የአመለካከት እንዲሁም የፓለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ያየንበት ነው ሲሉ ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።
ኮሚሽኑ በቀጣይ በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ፣ በእንግሊዝ፣ በሲውዲንና በዱባይ ተመሳሳይ መድረኮችን በማካሄድ አጀንዳዎችን እንደሚሰበስብ አሳውቋል።
በሄለን ተስፋዬ