ለክልሎች የሚተላለፈው የጋራ ገቢ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።
ምክር ቤቱ በገቢዎች ሚኒስቴር እና በማዕድን ሚኒስቴር ተሰብስቦ በቀመሩ መሠረት የሚተላለፈው የክልሎች ድርሻ በትክክል መድረሱን ለማረጋገጥ በተከናወነ የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት ግኝት ላይ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሚሰበሰበው የጋራ ገቢ ለክልሎች ለማስተላለፍ የሚሰላበት ቀመር ማሻሻያ እንደተደረገበት አስታውሰዋል።
ከማሻሻያው አስቀድሞ ክልሎች ከጋራ ገቢ የሚያገኙት ድርሻ 4.2 ቢሊዮን ብር ብቻ እንደነበረ ጠቁመው፤ አሁን ላይ መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ገልጸዋል።
እንደ አፈ-ጉባኤው ማብራሪያ፣ በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ከጋራ ገቢ ለክልሎች የሚከፋፈለው ድርሻ 91.73 ቢሊዮን ብር ደርሷል። በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሰባት ወራት ውስጥ ብቻ ከ71 ቢሊዮን ብር በላይ ማከፋፈል መቻሉ በመድረኩ ተመልክቷል።
የውይይት መድረኩ በኦዲት ግኝት ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር በመምከር፣ የሀብት ክፍፍሉ ፍትሐዊነትና ሕጋዊነትን ይበልጥ ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚቀጥል ታውቋል።
በሳምሶን ገድሉ