በሀገረ አሜሪካን በሚገኝ ሞጃቭ የተሰኘ በረሀ ላይ ዛሬም ድረስ ለበርካታ ዓመታት ያልተነሱ መኪናዎች ይገኛሉ።
እነዚህ የቮልስዋገን ምርት የሆኑ መኪናዎች ቁጥራቸው 300 ሺህ ይደርሳል። ከዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ከወራት ለበለጠ ጊዜ አልተነዱም።
ከፋብሪካ ከወጡ ጥቂት ወራት ብቻ ያስቆጠሩት መኪናዎቹ በረሀ ላይ ከቆሙ ዘጠኝ ዓመታትን አስቆጥረዋል።
እነዚህ አምስት አይነት ሞዴል ያላቸው መኪኖች ለዓመታት በዚህ ቦታ ለምን እንዲቆሙ ተደረገ?

የታሪኩ መነሻ እንዲህ ነው።
ቮልስዋገን እ.አ.አ. በ2015 “የዲዝልጌት ቅሌት” ተብሎ በሚጠራው እና በድርጅቱ ታሪክ አጋጥሞ በማያውቅ ችግር ውስጥ ገባ።
ኩባንያው አዲስ አምርቷቸው በነበሩት መኪኖች ላይ የአካባቢ ብክለትን የሚቀንስ ሶፍትዌር እንደገጠመ ገልጾ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መኪኖችን ለገበያ አቀረበ።
በጥቂት ወራት ውስጥም ቮልስዋገን በሚሊዮን የሚቆጠሩ መኪኖችን መሸጥ ቻለ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ የአሜሪካ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በመኪናዎቹ ላይ ባደረገው ምርመራ ተሽከርካሪዎቹ ላይ ተገጠመ የተባለው ሶፍትዌር ጥቅም የሌለው መሆኑን አረጋገጠ።
ከዚህ ባለፈ መኪናዎቹ የሚለቁት በካይ የጋዝ መጠንም በአሜሪካን ሕግ ከተፈቀደው በላይ መሆኑ ተደረሰበት።
ይህ ታላቅ የንግድ ማጭበርበር ይፋ እንደሆነም የቮልስዋገን ዝና መውደቅ ጀመረ።
በዚህ ብቻ አላበቃም በአሜሪካን የንግድ ሕግ መሰረት 300 ሺህ የሚሆኑ የተሸጡ መኪኖችን ከያሉበት እንዲመለሱ እና ኩባንያው የተለያዩ ቅጣቶችን እንዲከፍልም ተወሰነበት።
በዚህና በተለያዩ ምክንያቶች ካምፓኒው የ30 ቢሊዮን ዩሮ ክፍያም ተጥሎበት ነበር።
ቮክስዋገን ደንበኞቹ ያወጡትን ገንዘብ መልሶ የሰበሰባቸውን 300 ሺህ መኪናዎች በሞጃቭ በረሃ ውስጥ እንዲከማቹ አደረገ።
እነዚህ ከተሸጡ በጥቂት ወራት ውስጥ ተመልሰው የተሰበሰቡ አምስት አይነት ሞዴል ያላቸው መኪኖች የእያንዳንዳቸው ዋጋ ትንሹ 12 ሺህ ዶላር ሲሆን፤ ትልቁ ደግሞ 38 ሺህ ዶላር ነው።
ከዚህ በኋላም እ.አ.አ. በ2018 ቮልስዋገን ኸርበርት ዲስን የካምፓኒው ማናጀር አድርጎ ሾመ።
ይህ አዲስ ኃላፊ ቦታውን እንደያዘም ካምፓኒው ከደረሰበት ኪሳራ አገግሞ መቀጠል የሚችለው በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖችን ምርት በማቆም የኤሌትሪክ መኪናዎችን ማምረት ሲጀምር እንደሆነ አሳወቀ።
ከዚያም በርካታ ቢሊዮን ዶላሮችን በመመደብ ኩባንያውን ወደ ሥራው እንዲገባ አደረገ።
የኩባንያው አመራሮች ፋብሪካውን ሊያዘጋ ይችል በነበረው ክስተት እና የቢሊየን ዶላሮች ኪሳራ ተስፋ ሳይቆርጡ በዓለም ላይ የሚገኙት የድርጅቱ ማምረቻዎች በአብዛኛው የኤሌትሪክ መኪኖችን ብቻ እንዲያመርቱ ማድረግ ጀመሩ።
በጥቂት ዓመታት ውስጥም ቮልስዋገን በአየር ንብረት ጥበቃ ጉዳይ የተነሳ ያጣውን ስም መልሶ ማግኘት ጀመረ።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ቢሊየን ዶላሮችን ከስሮ፤ መልካም ስምና ዝናውንም አጥቶ የነበረው ቮክስዋገንም አንስራራ።
ምንም እንኳን ስህተቱ ዋጋ ቢያስከፍለውም፤ ከስህተቱ ተምሮ ፊቱን ወደ ኤሌትሪክ መኪና በማዞሩ ዛሬ ላይ በዓለማችን ካሉ ታላላቅ የኤሌትሪክ መኪና አምራቾች መካከል አንዱ ሆኗል።
ቮልስዋገንም አሁን ላይ ከቢዋይዲ እና ከቴስላ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ የሚገኝ ስኬታማ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ለመሆን መብቃቱን የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበውታል።