በአማራ ክልል ከደብረማርቆስ ወደ ባህርዳር በሚወስደዉ መንገድ በጊደብ ወንዝ ላይ የተሰራዉ ድልድይ በጎርፍ ተወስዷል፡፡
የምስራቅ ጎጃም ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዋለ አባተ አደጋው ሊደርስ የቻለው ሌሉቱን በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት መሆኑን ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል፡፡
በደረሰው አደጋ ምክንያት አሁን ላይ የትራንሰፖርት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ መቋረጡን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የደብረማርቆስ መንገድ ጥገና ዲስትሪክት ተገጣጣሚ ድልድይ በፍጥነት በመንገንባት ለአገልግሎት ለማብቃት እየሰራ መሆኑንም አቶ ዋለ ተናግረዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ የውላ ቀበሌ ውስጥ በሚገኘው ጌደብ ወንዝ ላይ በ1935 የተሰራው ይህ ድልድይ ከደብረማርቆስ ባህርዳር የሚወስድ ትልቅ መንገድ ነው።
መንገዱ ከፍተኛ የተሽከርካሪ ፍሠት ያለው በመሆኑ የመንገደኞች መስተጓጎል እንዳይፈጠር እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ደብረማርቆስ ዲስትሪክት አስታውቋል።
ችግሩ እንደተከሰተ በፍጥነት ጊዜአዊ ተገጣጣሚ የብረት ድልድይ እንዲገነባ የመንገዶች አስተዳደር ደብረማርቆስ ዲስትሪክት መረጃ ተሰጥቶ ከአዲስ አበባ እየተጫነ መሆኑን እና በቅርብ ጊዜ ለአገልግሎት እንደሚመቻች ነው ዲስትሪክቱ የገለጸው።
መንገዱ ለረጅም ጊዜ ያገለገለ በመሆኑ በቋሚነት የግንባታ በጀት ተይዞ እንዲጠገን ስለመጠየቁም ገልጿል።
በተመሳሳይ ከዓባይ በርሃ ጀምሮ እስከ ደጀን፣ ቢቸና፣ ደብረወርቅ፣ ፈለገብርሃን ድረስ ከዚህ በፊት አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የአስፓል መንገድ የተጎዳ ሲሆን ድልድዮችም በፍጥነት ካልተጠገኑ ተጨማሪ የሕዝብ መጉላላት መፈጠሩ አይቀርም ብሏል የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ደብረማርቆስ ዲስትሪክት።
ይህንንም በተደጋጋሚ ለመንገዶች አስተዳደር እያሳሰብን እንገኛለን ሲልም አክሏል።
በራሔል ፍሬው
#EBC #ebcdotstream #Bridge