Search

መደመር እና ዲፕሎማሲ - ኢትዮጵያ ዓለምን የምታይበት አዲስ መነጽር

ሓሙስ የካቲት 26, 2018 70

ዲፕሎማሲ የሀገርን ኅልውና እና ክብር የመጠበቂያ ትልቁ መሣሪያ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "መደመር" መጽሐፍ ላይ የተተነተነው የውጭ ግንኙነት እሳቤ፣ ኢትዮጵያ ከቀደሙት ዓመታት የተለየ አዲስ መንገድ መከተል እንዳለባት ያመለክታል።

የመደመር ዲፕሎማሲ ዓላማው ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ተሰሚነት ያላት፣ ክብሯ የተጠበቀ እና ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ የምታድግ ሀገር እንድትሆን ማድረግ ነው።

1.  ከ"ስጋት" ወደ "ብሔራዊ ክብር"

ቀደምት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶች በከፍተኛ ሁኔታ "በስጋት" ላይ የተመሠረቱ ነበሩ። "ጎረቤቶቻችን ሊወርሩን ይችላሉ" ወይም "ጠላት ከበበን" በሚል ፍርሃት ውስጥ የታጠሩ ነበሩ።

የመደመር እሳቤ ግን ይህንን ቀይሮ በራስ መተማመን ላይ የተመሠረተ፣ ብሔራዊ ጥቅምን እና የሀገርን ክብር ማዕከል ያደረገ ዲፕሎማሲ እንዲኖር ይሞግታል። አዲሱ አካሄድ የሀገራችንን ክብር ከታሪክ ድሎች ባለፈ በዘመናዊ ስኬቶች ማለትም በዴሞክራሲያዊ ሕጋዊነት እና በኢኮኖሚ ልማት መለካት እንዳለበት ያስገነዝባል።

2.  "እኔም ልጠቀም - አንተም ተጠቀም"

በዲፕሎማሲው ዓለም አንዱ ሲያተርፍ ሌላው የግድ መክሰር የለበትም፤ መደመር "በጋራ ተጠቃሚነት" ያምናል።

በተለይም በዓባይ ወንዝ እና በባሕር በር ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ የሌሎችን ጥቅም ሳትነካ የመጠቀም ፍላጎት አላት። የእርሷን ጥቅም ደግሞ አሳልፋ ሳትሰጥ የምታደርገው ድርድር የዚሁ እሳቤ አካል ነው።

የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት ግድቡ በማንም የውጭ ብድር ሳይሆን በሀገር ውስጥ ፋይናንስ መገንባቱ የሀገራችንን ዲፕሎማሲያዊ በራስ መተማመን ከፍ አድርጎታል። ኢትዮጵያ "በጋራ እንጠቀም" የሚለውን መርሕ በመያዝ፣ የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት ጥቅም ሳትነካ የራሷን የኤሌክትሪክ ፍላጎት የማሟላት መብቷን ለዓለም ማስመስከር ችላለች።

3.  የቀጣናዊ ትሥሥር 

"ጎረቤቴ ሰላም ካልሆነ ቤቴ ሰላም አይሆንም" በሚል መርሕ፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማት እና በፖለቲካ የመቀራረብ ሥራን ቅድሚያ ሰጥታለች።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ለጎረቤት ሀገራት የሚቀርበው ታዳሽ ኃይል እና የቀጣናዊ ትሥሥር ፕሮጀክቶች ናቸው። በተለይም ከኬንያ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ ጋር እየተፈጠረ ያለው ትሥሥር ለዘላቂ ሰላም መሠረት እየጣለ ይገኛል።

4.  ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ

ለዓመታት በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደ "ፖለቲካ ተቃዋሚ" ወይም እንደ "ዶላር ምንጭ" ብቻ ይታዩ ነበር። መደመር ግን ዳያስፖራውን የሀገር አምባሳደር እና የዕውቀት ምንጭ አድርጎ ይመለከታል። በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ከባዕድ ሀገር ወደ ቤት ማምጣት እና መብታቸውን ማስከበር የዲፕሎማሲው ቁልፍ ተግባር ተደርጎ ተቀምጧል፤ በተግባርም ታይቷል።

5.  ሚዛናዊ ግንኙነት

ዓለም በኃያላን መንግሥታት ሽኩቻ ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የአንደኛው ወገን ተከታይ ከመሆን ይልቅ ብሔራዊ ጥቅሟን ማዕከል ባደረገ "ሚዛናዊ ግንኙነት" ከሁሉም ጋር በትብብር መሥራትን መርጣለች።

የኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆን የዚህ ስትራቴጂካዊ ምርጫ ትልቁ ስኬት ነው። ይህ አባልነት ለሀገራችን ያለፖለቲካዊ ቅድመ-ሁኔታ በርካታ ድጋፎችን ከማስገኘቱም ባለፈ፣ የአፍሪካ እና የደቡባዊው ዓለም ድምፅ ሆና እንድትወጣ ትልቅ የጂኦፖለቲካ ተሰሚነት ሰጥቷታል።

ለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ:

ተያያዥ ዜናዎች: