የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኢትዮጵያ የኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ አባል እንድትሆን የተዘጋጀውን የማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርቷል።
ሀገራችን በዓለም አቀፍ የፋይናንስ መድረክ ላይ ያላትን ተደራዳሪነትና አማራጭ የመምረጥ አቅም በእጅጉ የሚያጠናክር አዲስ በር ተከፍቷል።
ይህ ታሪካዊ እርምጃ እንደ ዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ ካሉ ተቋማት ውጪ ያለምንም የፖለቲካ ቅድመ-ሁኔታና የሀገራትን ሉዓላዊነት ሳይጋፋ ግዙፍ የልማት ፋይናንስ ለማግኘት የሚያስችል ትልቅ ስትራቴጂካዊ እመርታ ነው።
በተለይም የፕሮጀክቶች ማፅደቅ ሂደት እጅግ ፈጣን መሆኑና ከ18 እስከ 24 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁ ለሀገራዊ ልማታችን ቀልጣፋ አማራጭ ይዞ የመጣ ነው።
የዚህ ታላቅ ባንክ አባል መሆን ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ በርካታ መዋቅራዊ ጥቅሞችን ያስገኝላታል። ባንኩ ብድሮችን በዶላር ብቻ ሳይሆን በአባል ሀገራቱ የሀገር ውስጥ ገንዘብ (ለምሳሌ በቻይና ዩዋን) የሚያቀርብ በመሆኑ፣ በሀገራችን ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የዶላር መዋዠቅ የሚያስከትለውን የዕዳ ጫና በእጅጉ ያቃልላል።
ይህ አስተማማኝ የፋይናንስ አቅርቦት ለቁልፍ መሠረተ-ልማቶች ማለትም ለግብርና ዘመናዊነት፣ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት፣ ለታዳሽ ኃይል ማመንጫዎች እና ለዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ፕሮጀክቶች የሚውል የረጅም ጊዜ ካፒታል በቀላሉ ለማግኘት ያስችላል።
ከዚህ ባለፈም ስምምነቱ አዲስ ለተጀመረው የሀገር ውስጥ የካፒታል ገበያ የቦንድ ሽያጭና የፋይናንስ ዋስትናዎችን በመስጠት ረገድ የላቀ አቅም የሚፈጥር ሲሆን፣ የቴክኒክ ድጋፍና የእውቀት ሽግግርን በማመቻቸት ተቋማዊ አቅማችንን ይገነባል።
ኢትዮጵያ የኒው ዴቨሎፕመንት ባንክን ለመቀላቀል እያደረገችው ያለው ስኬታማ ጉዞ ከብሪክስ አባል ሀገራት የምታገኘውን ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትና የንግድ ትስስር ወደ ላቀ ከፍታ የሚያሸጋግር በመሆኑ መላው ዜጋ ሊያውቀውና ሊረዳው የሚገባ ትልቅ የኢኮኖሚ ድል ነው።
በመሀመድ ፊጣሞ