የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በማስመለከት በአዲስ አበባ ከተማ ደማቅ የሴቶች የሩጫ ውድድር ተካሄደ።
የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በውድድሩ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሴቶች በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ውስጥ ያላቸው ሚና እና ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
የሩጫ ውድድሩ ለከተማዋ አዲስ ገጽታ በሆነውና በቅርቡ በተገነባው የኮሪደር መስመር ማለትም ከቦሌ ተርሚናል - አትላስ - ኡራኤል ተጀምሮ እስከ ሴቶች አደባባይ ድረስ ተከናውኗል። በዚህ ደማቅ ስፖርታዊ ኩነት ላይ ታዋቂ አትሌቶች፣ የውጭ ሀገር ዜጎችና በርካታ የመዲናዋ ሴቶች ተሳትፈዋል።
ከንቲባዋ በመልዕክታቸው እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ሴቶች በሀገሪቱ የብልፅግና እና የእኩልነት ጉዞ ላይ በንቃት በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። ይህ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና እኩል ተጠቃሚነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባዋ አረጋግጠዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመላው የከተማዋና የሀገሪቱ ሴቶች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።