Search

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሴቶችን አቅም በተግባር በማረጋገጥ ቀዳሚ ተምሳሌት ነው፦ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

እሑድ የካቲት 29, 2018 145

የኢትዮጵያ አየር መንገድ "ሴቶች በተወሰኑ የሥራ ዘርፎች ላይ ብቻ ይሳተፋሉ" የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት በመስበር ረገድ ግንባር ቀደም መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
አየር መንገዱ ሴቶችን ከአብራሪነት እስከ ቴክኒክ ጥገና፣ ከበረራ ቁጥጥር እስከ ከፍተኛ አመራርነት በማሳተፍ እያከናወነ ያለው ተግባር ለሌሎች የመንግሥትና የግል ተቋማት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
መንግሥት የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ የልማት ድርጅቶችና የፋይናንስ ተቋማትም ይህንን አርአያነት ያለው ተግባር እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሴቶች ተቋም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጃኔት ኪም በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሴቶች ብቻ የተመራ በረራ ማድረጉ ሴቶች ዕድልና ኃላፊነት ከተሰጣቸው ማንኛውንም ተግባር በብቃት እንደሚወጡ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በአቪዬሽን ዘርፍ ሴቶችን ለማብቃት በትኩረት መስራቱ የእኩልነት መርህን በተግባር ለዓለም ያሳየና የሚደነቅ ተግባር መሆኑን ዳይሬክተሯ አክለው ገልጸዋል። ይህ ሁሉንም ጾታ ያካተተ የሥራ እንቅስቃሴ የሀገሪቱን ብልጽግና ለማፋጠን ወሳኝ ሚና እንዳለው ተመልክቷል።
በቢታኒያ ሲሳይ