የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በድሬዳዋ አዲስ የፍተሻ ላቦራቶሪ አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤትን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡
ይህን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፤ ድርጅቱ ዓለም አቀፍ የአሰራር ስርዓትን በመከተል ለአምራቾች፣ ለአገልግሎት ሰጪዎች፣ ለላኪዎች፣ ለአስመጪዎች፣ ለተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶች፣ ለምርምር ተቋማትና ለሸማቹ ማህበረሰብ የምርትና አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎትን እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡
በድሬዳዋ አካባቢ ለሚገኙ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲሁም የደረቅ ወደብን መሰረት በማድረግ አዲስ የፍተሻ ላቦራቶሪ በማደራጀት አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረጉን ገልፀዋል።
ተቋሙ ከዚህ ቀደም በምግብ ዘይት፣ በነዳጅ ምርት፣ በተለያዩ የምግብ ምርቶች፣ ለማስዋቢያና የዲተርጀንት ምርቶች፣ ለኮንስትራክሽን ምርቶችና ግብዓቶች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡