አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ምርጫቸው ላደረጉ አዲስ ተማሪዎች እና ወላጆች የዩኒቨርሲቲ መረጃ ሳምንት ከነሐሴ 5 ጀምሮ መዘጋጀቱን የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ እና ተማሪዎችን በራሱ መቀበል ስለሚጠበቅበት ቀደም ብሎ ራሱን የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል።
ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚቀበሏቸው ተማሪዎች ምን ዓይነት ፕሮግራም እንዳላቸው፤ ስለሚሰጧቸው የትምህርት ዓይነቶች፤ ማደሪያ፣ መመገቢያ፣ ላቦራቶሪ፣ ላይብረሪ እና ሌሎች ግብዓቶችን ጨምሮ ስላላቸው መሠረተ ልማት ገለጻ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በራሱ መስፈርት ተማሪዎችን የሚቀበል በመሆኑ ራሱን የበለጠ የሚያስተዋውቅበት የዩኒቨርሲቲ መረጃ ሳምንት ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ተማሪዎች በዚህ የመረጃ ሳምንት ላይ ሲሳተፉ እያንዳንዱ የዩኒቨርሲቲው ኮሌጅ ምን ይዟል? የኮሌጁ መገኛ የት ነው? በእያንዳንዱ ኮሌጅ ሥር ያለው ፕሮግራም ምንድን ነው? በመጀመሪያ ዲግሪ እና በሁለተኛ ዲግሪ ምን ዓይነት ትምህርት አለ? በሚለው ላይ ግንዛቤ ያገኛሉ ብለዋል።
እንዲሁም በሕግ፣ በሕክምና፣ በኢንጂነሪንግ፣ በኢኮኖሚክስ፣ በአስተዳደር፣ በንግድ፣ በማኅበራዊ እና በተፈጥሮ ሳይንስ እና በሌሎች ዘርፎች ምን አለ? ትምህርቱ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል? የሚለው ላይ ሰፊ መረጃ የሚይዙበት እንደሆነም አብራርተዋል።
በመሆኑም ለ2018 የትምህርት ዘመን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ምርጫቸው ያደረጉ ተማሪዎች ከነሐሴ 05 ጀምሮ በሚካሄደው የመረጃ ሳምንት ላይ በመሳተፍ አስፈላጊውን መረጃ እንዲወስዱ ዶክተር ሳሙኤል ጋብዘዋል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት በመንግሥት ተመድበው በመሆኑ ይህ የመረጃ ሳምንት በሀገራችን ብዙም የተለመደ እንዳልነበር ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
ወደ ፊት ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ እና ተመራዎችን በራሳቸው መቀበል ሲጀምሩ ይህንኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጀመረውን አሠራር እንደሚከተሉ አስረድተዋል።
በዮናስ በድሉ
#EBC #ebcdotstream #AAU #education #University