Search

ጣናነሽ-፪ ከጅቡቲ ተነሥታ ባህር ዳር የደረሰችው በፍቅር ታጅባ ነው - አሽከርካሪው ሳምሶን ገ/ሥላሴ

ጣናነሽ-፪ ጀልባ ከጅቡቲ ተነሥታ ባህር ዳር በሰላም ለመድረሷ የሁሉም ኅብረተሰብ ተሳትፎ እና ያሳየው ፍቅር አስደናቂ ነበር ሲል ጀልባዋን የተሸከመው መኪና አሽከርካሪ ሳምሶን ገ/ሥላሴ ገለጸ። 

ሳምሶን፣ መነሻዋን ከጅቡቲ ዶራሌህ ወደብ መዳረሻዋን ደግሞ ባህር ዳር ጣና ሐይቅ ያደረገችውን ጣናነሽ-፪ን ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን አስቸጋሪውን መልክዓ-ምድር በማቆራረጥ ጀልባዋን የተሸከመውን መኪና በብቃት በማሽከርከር ከመዳረሻው አድርሷል።

 

አሽከርካሪው በጉዞው የነበረውን ገጠመኝ፣ ወጣ ውረዶችን እና ፈተናዎችን እንዴት ተሻግሮ ከመዳረሻዋ ባህር ዳር ማድረስ እንደተቻለ በእሑድ ቤት የቤት ለእንግዳ ዝግጅት ላይ ተሞክሮውን አጋርቷል።

ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ሲገነቡ ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግበዓቶችን ወደሚፈለገው አካባቢ የማድረስ ልምድ እና እውቀት ያካበተ መሆኑን የሚናገረው አሽከርካሪው ሳምሶን፤ ይህም አስቸጋሪውን መልክዓ-ምድር አቋርጦ ጣናነሽ-፪ ጀልባን ባህር ዳር ለማድረስ እንዳስቻለው በቆይታው ገልጿል።

ከጅቡቲ ተነሥቶ አፋር፣ ኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች እና አዲስ አበባን አቋርጦ ባህር ዳር በሰላም ለማድረስ መቻሉን የሚናገረው አሽከርካሪው፤ በደረሰበት ሁሉ ኢትዮጵያውያን ያሳዩት ክብር፣ ፍቅርና መተባበር እጅግ የተለየ ነበር ብሏል።

ጣናነሽ-፪ ጀልባን ባህር ዳር ለማድረስ በሚደረገው ፈታኝ ጉዞ ውስጥ የዓባይ በረሃን በሚታሰበው ፍጥነት አቋርጦ ለማለፍ ከጎሀጽዮን ጀምሮ እስከ ዓባይ ድልድይ ከዚያም እስከ ደጀን ያለው መንገድ ፈታኝ ነበር ነው ያለው። 

ካቋረጠው ረጅም ርቀት ሁሉ በተለይ የዓባይ በረሃ 10 ኪሎ ሜትር መንገድ እጅግ ፈታኝ እንደነበር ሳምሶን አንስቷል።

የፈጣሪ እርዳታ አልተለየኝም የሚለው ሳምሶን ጀልባዋን ዓባይ በረሃን ለማሻገር ከጎታች መኪናው ወርዶ በእግሩ በመራመድ የመንገዱን ሁኔታ እያረጋገጠ፣ እንቅፋቶችን እያስወገደ ይጓዝ እንደነበር ይገልፃል።

150 ሜትሪክ ቶን ክብደትና 38 ሜትር ርዝመት እንዲሁም 188 ሰዎችን የመጫን አቅም እንዳላት የሚነገርላት ጣናነሽ-፪ ጀልባን በሰላም ባህር ዳር ማድረስ መቻሉ ልዩ ስሜት እንደፈጠረበት ተናግሯል።

በአጠቃላይ ጣናነሽ-፪ን ወደ መዳረሻዋ የማጓጓዝ ሂደቱ እጅግ ፈታኝ የነበረ ቢሆንም በድል የተቋጨ፣ ለልጅ ልጆች የሚነገር ታሪክ ነው ብሏል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ትልቅና ዘመናዊ ጀልባ እንደሆነች የተነገረላት ጣናነሽ-፪ በደረሰችበት ክልልና የከተማ አስተዳደር ሁሉ የነበረው የህዝቡ አቀባበልና ፍቅር እጅግ አስገራሚ እንደነበር ሰምሶን ይገልፃል።

ጀልባዋን ወደ መዳረሻዋ በማጓጓዙ ተልዕኮ አብሮት ከነበረው ቻይናዊ ጓደኛው ጋር በየደረሱበት አካባቢና ከተማ ከህዝቡ ያልጠበቁትን የአክብሮት አቀባበል በማግኘታቸው አግራሞትን እንደፈጠረባቸውም ይናገራል።

ጣናነሽ-፪ ጀልባ በቅርቡ በባህር ዳር ጣና ሐይቅ ተሰማርታ ለጎብኚዎች እና ለነዋሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ትሰጣለች ተብሎ ይጠበቃል።

በመሐመድ ፊጣሞ

#ኢቢሲ #ኢቲቪ #ኢቢሲዶትስትሪም #ጣናነሽ2 #ሳምሶንገብረሥላሴ