Search

"ጎርፍ ልጆቼን እንዳይወስድብኝ በመስጋት ቁጭ ብዬ አድር ነበር፤ አሁን የሰላም እንቅልፍ እተኛለሁ" - የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚዋ

በትራቀች ሸሪፍ የአብነት አካባቢ ነዋሪ ስትሆን የሁለት ልጆች እናት ናት።

ባለቤቷ ባጋጠመው የጤና እክል ቤቱን ማስተዳደር ባለመቻሉ የቤተሰቧ ሙሉ ሀላፊነት በእርሷ ላይ ይወድቃል።

እናም ልጆችዋን ለማስተማር እና የዕለት ጉርስ ፍለጋ በየሰዉ ቤት ልብስ እያጠበች፣ በጉልት እየቸረቸረች ኑሮዋን መደጎም ትጀምራለች።

በትራቀች በዚህ ሁኔታ ጥቂት ከቆየች በኋላ ባጋጠማት የጤና እክል ሥራ ለመሥራት ትቸገራለች።

ከቤተሰቧ ጋር የምትኖርበት ቤትም በጣም ያረጀ እና ለጎርፍ በመሆኑ ክረምት በመጣ ቁጥር ከላይ ፍሳሹ ከታች ደግሞ ጎርፉ ያሳቅቃት እንደነበር ትናገራለች።

"የወደቀ ቤት ነው የነበረኝ፤ ዝናብ ሲዘንብ ጎረቤቶቼ ጎርፍ እንዳይወስደኝ ይሰጉ ነበር፤ እኔ ደግሞ በተኛሁበት ጎርፍ ድንገት ልጆቼን እንዳይወስድብኝ በመስጋት እየጠበቅኳቸው ቁጭ ብዬ አድር ነበር" ትላለች።

ይህን የተገነዘቡት የአብነት የማህበረሰብ ት/ቤቶች ታዲያ የአብነት ወረዳን የግንባታ ፈቃድ ጠይቀው ያረጀ ቤቷን አፍርሰው መልሰው በመገንባት ከፍሳሹም ከጎርፉም እፎይ እንደሰኟት ነው በትራቀች የምትገልጸው። ት/ቤቶቹ ከእርሷ በተጨማሪ የሌሎች አቅመ ደካሞችን ቤቶች ጭምር መገንባታቸውንም ጠቅሳለች።

የአብነት የማህበረሰብ ት/ቤቶች ቤቴን ከማደስ ባለፈ ለልጆቼ ነፃ የትምህርት ዕድል እና በየወሩ የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉልኝ ነው፤ አሁን ዝናብ እየዘነበም ቢሆን የሰላም እንቅልፍ እተኛለሁ፣ ድንገት ጎርፍ ቢገባስ ብዬም አልሰጋም ስትል ገልፃለች።

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚዋ በትራቀች ሸሪፍ በተለያየ የማህበራዊ ሀላፊነት እና የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ በንቃት ለሚሳተፉት የአብነት የማህበረሰብ ት/ቤቶች በምርቃት የታጀበ ምስጋናዋን አቅርባለች።

በሄለን ተስፋዬ

#ኢቲቪ #ኢቢሲዶትስትሪም #ክረምት #የበጎፈቃድአገልግሎ #የማህበረሰብአገልግሎት